ሄዝቦላህ ከ80 በላይ ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኮሰ
የሊባኖሱ ቡድን የተኮሳቸው ሮኬቶች በተለይ ኪርያት ሽሞና የተባለችው ከተማ ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ተገልጿል
ሄዝቦላህ የእስራኤል ጄቶች በፈጸሙት ድብደባ ለደረሰው ጉዳት የአጻፋ እርምጃውን እንደሚቀጥል ዝቷል
የደቡባዊ እስራኤል ከተማዋ ኪርያት ሺሞና የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የሮኬት ጥቃት ኢላማ ሆና ከፍተኛ ጉዳት ማስተናገዷ ተገለጸ።
ሄዝቦላህ ትናንት ምሽት ከ50 በላይ ሮኬቶችን ወደ ከተማዋ መተኮሱን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
አብዛኞቹ ሮኬቶች ተመተው መውደቃቸውን የገለጸው ጦሩ፥ የተወሰኑት ጉዳት ማድረሳቸውን ባወጣው መግለጫ አመላክቷል።
ታይምስ ኦፍ እስራኤል የኪርያት ሽሞና ከተማ ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው አንድ ሮኬት ህንጻ የመታ ሲሆን፥ ሌላ ሮኬት ደግሞ መንገድ ላይ ወድቆ ጉዳት አድርሷል።
ዛሬ ማለዳ 30 ሮኬቶች ከሊባኖስ ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን የገለጸው የእስራኤል ጦር የደረሰውን ጉዳት አልጠቀሰም።
ሄዝቦላህ ባወጣው መግለጫ ለሮኬት ጥቃቶቹ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ማስታወቁን ሲጂቲኤን አስነበቧል።
ቡድኑ ጥቃቱን የፈጸመው የእስራኤል ጄቶች በትናንትናው እለት በደቡባዊ ሊባኖስ ፍሩን በተባለች ከተማ ላደረሱት ጉዳት አጻፋዊ እርምጃ ለመውሰድ ነው።
ሄዝቦላህ ሶስት ሲቪል ሰራተኞች ለተገደሉበትና ሁለት ሰዎች ለቆሰሉበት ጥቃት የሚወስደው የበቀል እርምጃ እንደሚቀጥልም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
የእስራኤል ጦር ሄዝቦላህ በደቡባዊ ሊባኖስ ኤታሩን፣ ማሩን አል ራስ እና ያሩን በተባሉ ከተሞች የሚጠቀምባቸውን ህንጻዎች ሲደበድብ ማምሸቱን ገልጿል።
በፋሩን ከተማ የተገደሉት ሰዎችም የሄዝቦላህ ክንፍ የሆነው “አማል ንቅናቄ” አባል ናቸው ብሏል።
ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ሲገልጽ የቆየው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ለወራት ወደ እስራኤል ከተሞች ሲተኩስ ቆይቷል።
እስራኤልም ከኢራን ድጋፍ ያገኛል በምትለው ቡድን ይዞታዎች ላይ የአየር ድብደባዋን ቀጥላለች።