ሶስት እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ድንበር ተገደሉ
ግድያውን ያወገዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጥቃቱን ከኢራንና ከምታስታጥቃቸው ሃይሎች ጋር አገናኝተውታል
ዮርዳኖስ ከዌስትባንክ ጋር በሚያዋስናት የድንበር መተላለፊያ የተፈጸመውን ጥቃት እየመረመርኩ ነው ብላለች
ሶስት እስራኤላውያን በዮርዳኖስ እና ዌስትባንክ መተላለፊያ ድንበር ተተኩሶባቸው ተገደሉ።
እያሽከረከረ ከወደ ዮርዳኖስ ወደ ዌስትባንክ የገባው ግለሰብም በጸጥታ ሃይሎች መገደሉን የእስራኤል ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ህይወታቸው ያለፈው እስራኤላውያን እድሜያቸው ከ50 አመት በላይ የሆነ ወንዶች መሆናቸውን የእስራኤል አስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ተቋም ገልጿል።
ዮርዳኖስ “አለንቢ” በተሰኘው መተላለፊያ የተፈጸመውን ግድያ እየመረመርኩ ነው ማለቷን የሀገሪቱ ብሄራዊ የዜና ወኪል ፔትራ ኒውስ አስነብቧል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግድያውን አጥብቀው ያወገዙት ሲሆን፥ ከኢራን እና ከምታስታጥቃቸው ሃይሎች ጋር የሚገናኝ ጥቃት ነው ብለዋል።
በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ የተገነባው የአለንቢ መተላለፊያ “ንጉስ ሁሴን ድልድይ” እየተባለ የሚጠራ ሲሆን፥ እስራኤላውያን፣ ፍልስጤማውያን እና አለማቀፍ ጎብኝዎች ይጠቀሙታል።
የጋዛው ጦርነትን ተከትሎ እስራኤል እና ዮርዳኖስ መተላለፊያውን ለመዝጋት ወስነው የነበረ ሲሆን፥ እስራኤል ከዮርዳኖስ ጋር የሚያዋስናትን የየብስ ድንበር ዘግታ እንደነበር ፍራንስ 24 አስታውሷል።
ዮርዳኖስ በ1994 ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ ከምዕራባውያን ጋር ወዳጀነት ከመሰረቱ የአረብ ሀገራት መካከል አንዷ ነበረች።
በርካታ ፍልስጤማውያን የሚኖሩባት አማን በጥቅምት ወር እስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከጀመሩ በኋላ ተደጋጋሚና ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደውባታል።
ዮርዳኖስ ከወራት በፊት ኢራን ወደ እስራኤል ሚሳኤሎችን ስታዘንብ ለቴል አቪቭ አጋዥ መሆኗ ወቀሳ አስነስቶባት ነበር።
አማን ከ300 በላይ የኢራንን ድሮኖችና ሚሳኤሎች በማክሸፉ ሂደት ትልቅ ሚና መጫወቷ ከቴህራን ከባድ ማስጠንቀቂያ አስከትሎባት እንደነበርም አይዘነጋም።