ኔታንያሁ “ቅዠት” ነው ያሉት የሃማስ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ምን ምን አካቷል?
ሃማስ በጋዛ ለ135 ቀናት ተኩስ በማቆም በሶስት ምዕፎች የሚተገበሩ ጉዳዮችን ይፋ አድርጓል
እስራኤል ግን ብቸኛው መንገድ ሃማስን ሙሉ በሙሉ ድል ማድረግ ነው ብላለች
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስት ቤንያሚን ኔታንያሁ በሃማስ የቀረበውን የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ውድቅ አደረጉ።
ሃማስ ለ135 ቀናት ተኩስ በማቆም ታጋቾችን ለመልቀቅና ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል ያለውን እቅድ በትናንትናው እለት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
እስራኤልና ሃማስን በማደራደር ላይ የምትገኘው ኳታር የፍልስጤሙ ቡድን ተኩስ ለማቆም “አዎንታዊ ምላሽ” መስጠቱን በገለጸች ማግስት ቴል አቪቭ ከቡድኑ ጋር ምንም አይነት ድርድር እያደረግኩ አይደለም ብላለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ የሃማስን ቅድመ ሁኔታዎች “ቅዠት” ናቸው ያሉ ሲሆን፥ ብቸኛው አማራጫችን ቡድኑን ሙሉ በሙሉ መደምሰስ ነው ማለታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
“ሃማስ በጋዛ ህልውናው ከቀጠለ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሌላ ጭፍጨፋ መከሰቱ አይቀርም” ያሉት ኔታንያሁ፥ ሀገራቸው በጋዛ ቡድኑን ድል እስክታደርግ ድረስ ለወራት ጦርነቱን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
የሃማስ ከፍተኛ አመራር ሳሚ አቡ ዙህሪ፥ የኔታንያሁ አስተያየት ጦርነቱን ቀጠናዊ መልክ የማስያዝ “አጉል ፖለቲካዊ ጀብደኝነት” ነው ይላሉ።
የግብጽ ባለስልጣናት በበኩላቸው የእስራኤልና ሃማስ ልኡካን በካይሮ ከዛሬ ጀምሮ አዲስ ድርድር እንደሚጀምሩና ሁለቱም አካላት አቋማቸውን አለዝበው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል።
በሃማስ የቀረበው ባለሶስት ምዕራፍ የተኩስ አቁም ሃሳብ ምን ይላል?
ምዕራፍ 1 ፦ ለ45 ቀናት ተኩስ ቆሞ ሴቶች፣ ከ19 አመት በታች ወንዶች፣ አዛውንቶችና የታመሙ እስራኤላውያን ታጋቾች ይለቀቃሉ፤ በምትኩም በእስራኤል እስርቤቶች የሚገኙ ፍልስጤማውያን ይፈታሉ። የእስራኤል ጦር ህዝብ በብዛት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ወጥቶ የሆስፒታሎች እና የስደተኞች ጣቢያዎች ዳግም ግንባታ ይጀመራል።
ምዕራፍ 2 ፦ ቀሪዎቹ ታጋቾች ተለቀው እስራኤልም ሙሉ በሙሉ ከጋዛ ትወጣለች።
ምዕራፍ 3 ፦ በሁለቱም በኩል የተገደሉ ሰዎች አስከሬን ልውውጥ ይደረጋል።
የሃማስ የተኩስ አቁም ምክረሃሳብ ለ135 ቀናት የሚተገበር ሲሆን በጋዛ ምግብና ሌሎች ድጋፎች በፍጥነት እንዲገቡም የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
ከ27 ሺህ 700 በላይ ፍልስጤማውያንን የቀጠፈውና ከ65 ሺህ በላዩን ያቆሰለው ጦርነት ይቆም ዘንድ በሃማስ የቀረበውን እቅድ ግን እስራኤል በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብላዋለች።