እስራኤል ልዩ ዘመቻ በማካሄድ ሁለት በሃማስ ታግተው የነበሩ ዜጎቿን ማስለቀቋን ገለጸች
በራፋህ በሚገኝ ህንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ታግተው የነበሩትን እስራኤላውያን ለማስለቀቅ ከባድ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል
እስራኤል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን በሰፈሩበት ራፋህ ጥቃት እየፈጸመች ነው
እስራኤል ልዩ ዘመቻ በማካሄድ ሁለት ታጋች ዜጎቿን ማስለቀቅ መቻሏን አስታወቀች።
በራፋህ በሚገኝ አንድ ህንጻ ሁለተኛ ፎቅ ላይ ታግተው የነበሩትን የ60 አመቱ ፈርናንዶ ሲሞን ማርዋን እና የ70 አመቱ ሉይስ ሃር ለማስለቀቅ በአየር ጥቃት የታገዘ ልዩ ዘመቻ ተካሂዷል።
ህንጻው ላይ ፈንጂዎች ተጠምደው እንደነበርና ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መደረጉንም ነው የእስራኤል ጦር የገለጸው።
ታጋቾቹን ለማስለቀቅ የእስራኤል ጦር፣ የደህንነት ተቋሙ (ሺን ቤት) እና የእስራኤል ፖሊስ በጋራ መሳተፋቸውም ተጠቁሟል።
ከእገታ ነጻ የወጡት እስራኤላውያን ወደ ሀገራቸው ተወስደው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፥ በጥሩ ጤንነት ላይ ናቸው ተብሏል።
ታጋቾቹን የማስለቀቁን ዘመቻ “አስደናቂ” ነው ያሉት የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮቭ ጋላንት፥ “ታግተው የሚገኙ ዜጎቻችን ለማስለቀቅ የትኛውንም አማራጭ እንጠቀማለን” ብለዋል።
እስራኤል በጦርነቱ ምክንያት ከመኖሪያ ቀያቸው የሸሹ ፍልስጤማውያን በሚገኙበት ራፋህ የምትወስደውን እርምጃ ማጠናከሯን ሬውተርስ ዘግቧል።
በራፋህ ባለፉት 24 ስአታት ብቻ 37 ፍልስጤማውያን መገደላቸውንም ነው የገለጸው።
አጃንድ ፍራንስ ፕሬስ በበኩሏ የሟቾቹ ቁጥር 52 መሆኑን የጋዛ የጤና ሚኒስቴርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
ከትናንት በስቲያም 112 ፍልስጤማውያን በራፋህ በተፈጸሙ ጥቃቶች ህይወታቸው ማለፉ መገለጹ ይታወሳል።
እስራኤል ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያን የሰፈሩበትን ራፋህ ኢላማ አድርጋ የምትፈጽምው ጥቃት ከባድ ቀውስ ይፈጥራል በሚል አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።
ሃማስ በበኩሉ እስራኤል የሰብአዊ ድጋፍ የሚገባበትን ራፋህ መደብደቧን መቀጠሏ ምንም መሸሸጊያ የሌላቸውን ፍልስጤማውያን”ዘር ለማጥፋት” የያዘችው እቅድ ማሳያ ነው ብሏል።
በአሁኑ ወቅት ካን ዩኒስና ራፋህ ላይ ትኩረት ያደረገው የእስራኤላና ሃማስ ጦርነት 129ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፥ የ28 ሺህ 100 ፍልስጤማውያንን ህይወት ቀጥፎ ከ67 ሺህ 500 በላይ ሰዎችን አቁስሏል።