በጦርነት ወቅት ህይወታቸው የተቀጠፈ ህጻናት
በጋዛ በአራት ወራት የተገደሉ ህጻናት ቁጥር በአራት አመታት በመላው አለም ከሞቱት ይበልጣል
ተመድ በጋዛው ጦርነት ከሞቱት ከ31 ሺህ በላይ ሰዎች 40 በመቶው ህጻናት መሆናቸውም አሳሳቢ ነው ብሏል
የመንግስታቱ ድርጅት በጋዛ እያለቁ የሚገኙ ህጻናት ቁጥር አስደንጋጭ መሆኑን ገልጿል።
በአራት ወራት ውስጥ በጋዛ የተገደሉ ህጻናት ቁጥር በአራት አመታት ውስጥ በመላው አለም በጦርነት ምክንያት ህይወታቸው ካለፈው ህጻናት እንደሚልቅም ነው ያስታወቀው።
በተመድ የፍልስጤም የእርዳታ ኤጀንሲ ኮሚሽነር ፊሊፒ ላዛሪኒ እንደተናገሩት፥ ከ2019 እስከ 2022 ዩክሬንን ጨምሮ ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተገደሉ ህጻናት ቁጥር 12 ሺህ 193 ነው።
ከህዳር 2023 እስከ የካቲት 2024 ባሉት አምስት ወራት ብቻ ደግሞ 12 ሺህ 300 ፍልስጤማውያን ህጻናት በእስራኤል ድብደባ መገደላቸውንም ጠቅሰዋል።
በጋዛ የተገደሉ ህጻናት ቁጥር በትናንትናው እለት 13 ሺህ 500 መድረሱንም የጋዛ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በጦርነቱ ህይወታቸው ካለፈ ከ31 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን ውስጥ ከ70 በመቶ በላዩ ሴቶችና ህጻናት ናቸው።
ከ40 በመቶ በላዩ የጦርነቱ ሰለባዎች ህጻናት መሆናቸው እስራኤልን “በህጻናትና በፍልስጤም መጻኢ ተረካቢ ላይ ያነጣጠረ ጦርነት” አውጃለች የሚሉ ወቀሳዎች እንዲነሱባት አድርጓል።