እስራኤል በፍልስጤም ራስገዝ አስተዳደር ዋና ከተማ ራማላህ ላይ ከባድ ወረራ ፈጸመች
የእስራኤል ጦር እንደሚለው ከሆነ ወረራ ባካሄደበት ወቅት ፍልስጤማውያን ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ፔትሮል ቦምብ በመወርወራቸው ግጭት ተፈጥሯል
የእስራኤል ጦር አማሪ በተባለው የስደተኞች ካምፕ ላይ ባደረሱት ጥቃት የ16 አመት ልጅ መግደላቸውን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል
እስራኤል በፍልስጤም ራስገዝ አስተዳደር ዋና ከተማ ራማላህ ላይ ከባድ ወረራ ፈጸመች።
የእስራኤል ጦር ከአመታት ወዲህ በዌስትባንክ ውስጥ ያለችውን የፍልስጤም ራስገዝ አስተዳደር ዋና ከተማ ራማላህን በመውረር በስደተኞች ካምፕ ውስጥ የ16 አመት ልጅ መግደላቸውን የፍልስጤም ምንጮችን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የእስራኤል ጦር እንደሚለው ከሆነ ወረራ ባካሄደበት ወቅት ፍልስጤማውያን ተቃዋሚዎች ድንጋይ እና ፔትሮል ቦምብ በመወርወራቸው ግጭት ተፈጥሯል።
ሮይተርስ የአይን ምስክሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል ጦር አባላት የተወሰነውን የዌስትባንክ ክፍል ወደሚያስተዳድረው የፍልስጤም አስተዳደር በደርዘን የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎችን እየነዱ ገብተዋል።
የእስራኤል ጦር አማሪ በተባለው የስደተኞች ካምፕ ላይ ባደረሱት ጥቃት ሙስጠፋ አቡ የተባለ የ16 አመት ልጅ መግደላቸውን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የፍልስጤም ዜና አገልግሎት የእስራኤል ጦር ካምፑን ጥሰው በመግባታቸው ግጭት መፈጠሩን እና በፍልስጤማውያን ወጣቶች ላይ ጥይት መተኮሱን ዘግቧል።
ነገርግን የእስራኤል ጦር እንደገለጸው የጸጥታ ኃይሎች በካምፑ ላይ ለስድስት ሰአታት የቆየ የጸረ-ሽብር ዘመቻ አድርገው ሁለት ተጠርጣሪዎችን እና በሃማስ የተሰራጩ ግጭት ቀስቃሽ መልእክቶችን ይዟል።
"በዘመቻው ወቅቷ ግጭት ተቀስቅሶ ተጠርጣሪዎች ድንጋይ እና ሞሎቶቭ ኮክቴል ወደ ጸጥታ ኃይሎች ሲወረውሩ፣ የጸጥታ ኃይሎችም ጥይት ተኩሰዋል" ብሏል ጦሩ።
በዚህ ግጭት የእስራኤል የድንበር ጥበቃ ፖሊስም ቀላል ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል።
የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበከሉ የእስራኤል ባለስልጣናት በመውረር፣ በመደብደብ፣ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል እና በማሰር በዌስትባንክ የፍልስጤማውያን ህይወት "ሲኦል" እንዲሆን አድርገውታል ሲል ገልጿል።