እስራኤል ፍልስጤማውያንን ከራፋህ ማስወጣት ልትጀምር ነው
ፍልስጤማውያኑን ከአለማቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር በሚቋቋሙ “ሰብአዊ ደሴቶች” ለማስፈር ማቀዷንም ነው ያስታወቀችው
የእስራኤል ጦር በራፋህ መሽገዋል ያላቸውን ከ4 ሺህ በላይ የሃማስ ታጣቂዎች ለመደምሰስ የእግረኛ ጦር መግባቱ አይቀሬ ነው ብሏል
እስራኤል በደቡባዊ ጋዛ ራፋህ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ፍልስጤማውያንን ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር እየሰራች መሆኑን ገለጸች።
ጦርነቱን ሸሽተው ራፋህን በዳስ የሞሉት ፍልስጤማውያን ወደ “ሰብአዊ ደሴቶች” ከተዘዋወሩ በኋላ ከሃማስ ጋር ጦርነቱ እንደሚጀመርም ነው የእስራኤል ጦር ያስታወቀው።
የጦሩ ቃል አቀባይ ዳኔል ሃጋሪ “ሰብአዊ ደሴቶች” ያሉት ፍልስጤማውያን የሚሰፍሩበት አካባቢ የት እንደሚገኝና ከመቼ ጀምሮ ከራፋህ የማስወጣቱ ስራ እንደሚጀምር አላብራሩም።
ከአለማቀፉ ማህበረሰብ ጋር በትብብር ይከናወናል ያሉት ፍልስጤማውያኑን ከራፋህ የማስወጣት ስራ ተጠናቆ ወታደራዊ ዘመቻው መቼ እንደሚጀመርም በመግለጫቸው አልጠቀሱም።
“ደሴቶቹ ከራፋህ ለሚወጡት ፍልስጤማውያን ጊዜያዊ መጠለያ፣ ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ያቀርባሉ” ያሉት ቃል አቀባዩ፥ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየኑ ነዋሪ አብዛኛው እንደሚወጣ ተናግረዋል።
በራፋህ ወረራ ዙሪያ ስጋት እንዳላት ስትገልጽ የቆየችው አሜሪካ በበኩሏ ቴል አቪቭ ፍልስጤማውያንን ከራፋህ የምታስወጣበትን እቅድ እስካሁን አልተመለከትኩም ብላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን “በራፋህ ወታደራዊ ዘመቻ ለመጀመር ንጹሃንን ከአደጋ የሚጠብቅ ግልጽ እቅድ መቅረብ አለበት፤ እስካሁን ይህን አልተመለከትንም” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
ጦርነቱ እንደተጀመረ እስራኤል ፍልስጤማውያን ወደ ጋዛ የሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ እንዲያመሩ ሲያደርጉ ነበር። አካባቢው ከጦርነት ቀጠና የራቀ ቢሆንም ገና አልለማም።
እስራኤል ከራፋህ የሚወጡ ሰዎችን በዚህ ለማስፈር ግን ትቸገራለች ብለዋል የእርዳታ ድርጅቶች። ሰላማዊ ነው የተባለው አካባቢ በእስራኤል የድብደባ ኢላማ ውስጥ መግባቱንና ሚሊየኖችን ማስተናገድ እንደማይችልም በመጥቀስ።
የእስራኤል ጦር በራፋህ መሽገዋል ያላቸውን ከ4 ሺህ በላይ የሃማስ ታጣቂዎች ለመደምሰስ ንጹሃኑን የማስወጣቱ ስራ በፍጥነት ይከናወናል ቢልም የሚሰፍሩበትን ቦታ አልገለጸም።
ይህም እስራኤል ፍልስጤማውያንን ወደ ሲናይ በርሃ የማስገባት ውጥን አላት ለምትለው ግብጽ ጥርጣሬን የፈጠረ ሆኗል።