እስራኤል በዌስትባንክ 3 ሺህ 400 ቤቶችን ለመገንባት የወጣውን እቅድ አጸደቀች
የፍልስጤም አስተዳደር ቴል አቪቭ ከሰኔ ወር 2023 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጸደቀችውን የሰፈራ እቅድ አውግዞታል
እስራኤል በሀይል በያዘቻቸው ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ከ700 ሺህ በላይ አይሁዳውያንን ማስፈሯ ይታወሳል
እስራኤል በዌስትባንክ 3 ሺህ 400 አዳዲስ ቤቶችን ለመገንባት የወጣውን እቅድ አጸደቀች።
ከእቅዱ 70 በመቶ ቤቶች በምስራቅ እየሩሳሌም ማል አዱሚም በተባለ አካባቢ ይገነባሉ የተባለ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በደቡባዊ ቤተልሄም ኬዳር እና ኢፍራት በተባሉ ስፍራዎች እንደሚገነቡ ተገልጿል።
የእስራኤሉ የፋይናንስ ሚኒስትር ቤዛለል ስሞትሪች ባለፈው አመት ብቻ በዌስትባንክ 18 ሺህ 515 የሰፈራ ቤቶችን መገንባት የሚያስችሉ እቅዶች መጽደቃቸውን አስታውሰዋል።
“ጠላቶቻችን እኛን ለማዳከም ቢሞክሩም በዚህ መሬት ላይ መገንባታችን ይቀጥላል” ሲሉም በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በየካቲት ወር መጨረሻ ሶስት ፍልስጤማውያን በማል አዱሚም በተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ከፍተው አንድ እስራኤላዊ የተገደለበትንና በርካቶች የቆሰሉበትን ጥቃት አስታውሰውም፥ የጸጥታ ሃይሉን ከማጠናከር ባሻገር “የሰፈራ ምላሽ” መስጠት ይገባል ማለታቸውንም ቢቢሲ ዘግቧል።
እስራኤል በሃይል በያዘችው የፍልስጤም መሬት ላይ የምታከናውነውን የሰፈራ ፕሮግራም የሚቃወመው የእስራኤሉ “ፒስ ናው” በበኩሉ፥ “የእስራኤል መንግስት ለመጻኢ ተስፋ፣ ሰላምና ደህንነት ከመስራት ይልቅ የምንወድምበትን መንገድ እየጠረገ ነው” ሲል ውሳኔውን ተቃውሞታል።
በዌስትባንክ የሚካሄዱ የሰፈራ ቤቶች ግንባታ የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭትን ለመቋጨት ይረዳል የተባለውን የሁለት መንግስታት መፍትሄ ወይም “ቱ ስቴት ሶሊዩሽን” ተግባራዊ ማድረግ አያስችልም ነው ያለው።
በዌስትባንክ የሚገኘው የፍልስጤም አስተዳደር (ፒኤ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አዲሱ የሰፈራ እቅድም ሆነ የሚኒስትሩ ንግግር ውጥረቱን የሚያባብስ ነው በሚል አጥብቆ አውግዞታል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው፥ እስራኤል የሰፈራ ፕሮግራሟን ለመቀጠል በመወሰኗ በመወሰኗ ቅሬታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አሜሪካ የእስራኤልን የሰፈራ ፕሮግራም “ህገወጥ” ነው ብላ እንደምታምን መናገራቸውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በ2019 ካሳለፉት ውሳኔ በተቃርኖ የቆመ ነው ተብሏል።
ብሊንከን እስራኤል በዌስትባንክ የቤቶች ግንባታዋን ማስፋፋቷ ደህንነቷን ቢያዳክም እንጂ የሚያጠናክር አይደለም ሲሉም ነው በአርጀንቲና ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ያብራሩት።
እስራኤልና ሃማስ ከጥቅምት ወር ጀምሮ ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ እስራኤላውያን በሰፈሩባቸው ዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ግጭቶች ተከስተዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዌስትባንክ እና ምስራቅ እየሩሳሌም ከ413 በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል። 15 እስራኤላውያንም በግጭቱ ህይወታቸው አልፏል።
እስራኤል በ1967ቱ የስድስት ቀናት ጦርነት በሃይል በተቆጣጠረቻቸው የፍልስጤም የቀድሞ ግዛቶች ዌስት ባንክ እና ምስራቅ ኢየሩሳሌም ቤቶች ገንብታ 700 ሺህ አይሁዳውያንን ማስፈሯ ይታወሳል።
ድርጊቱ አለማቀፍ ህግን የሚጥስ መሆኑን ሀገራትና ተቋማት ቢገልጹም ቴል አቪቭ የሰፈራ ፕሮግራሟን አላቋረጠችም።