እስራኤል ኢምባሲ ደጃፍ ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው ወታደር በፍልስጤም በስሙ መንገድ ተሰየመለት
ቡሽኔል ራሱን አቃጥሎ የገደለው አሜሪካ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወረራ መደገፏን በመቃወም ነው
የጀሪቾ ከተማ ከንቲባ የሟች ወታደር አሮን ቡሽኔል ስም የተጻፈበትን የመንገድ ምልክት ህዝብ በተሰበሰበበት ይፋ አድርገዋል
በዋሽንግተን እስራኤል ኢምባሲ ደጃፍ ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው ወታደር በፍልስጤም በስሙ መንገድ ተሰይሞለታል።
በፍልስጤም ዌስት ባንክ ውስጥ የምትገኘው ከተማ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወረራ በመቃወም ራሱን በእሳት አቃጥሎ በገደለው የአሜሪካ ወታደር ስም መንገድ መሰየሟ ተገልጿል።
በላፈው እሁድ እለት የጀሪቾ ከተማ ከንቲባ የሟች ወታደር አሮን ቡሽኔል ስም የተጻፈበትን የመንገድ ምልክት ህዝብ በተሰበሰበበት ይፋ አድርገዋል።
በአሜሪካ አየር ኃይል ውስጥ ያገለግል የነበረው ቡሽኔል ባለፈው ወር በዋሽንግተን እስራኤል ኢምባሲ ደጃፍ ራሱን አቃጥሎ የገደለው አሜሪካ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወረራ መደገፏን በመቃወም ነው።
ቡሽኔል በጋዛ እየተፈጸመ ባለው "የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ከዚህ በኋላ አልተባበርም"ሲልም ተደምጧል።
የጀሪቾ ከተማ ከንቲባ አብዱል ከሪም ስድር ቡሽኔል" ሁሉንም ነገር መስዋት" አድርጓል ብለዋል።
ከንቲባው አክለውም "እኛ አናውቀውም፤ እሱም አያውቀንም። የማህበራዊ፣ ፓለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት በመካከላችን የለም። የምንጋራው ነጻነትን መውደድን እና እየተጠቁ ላሉት መቆምን ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የ25 አመቱ ቡሽኔል ራሱን በእሳት ያያዘበትን እና ተቃውምውን ያሰማበትን ሁነት በማህበራዊ ሚዲያ በቀጥታ አስተላልፎ ነበር።
በኢምባሲው ደጃፍ የነበሩ የሰክሬት ሰርቪስ አባላት ደርሰው እሳቱን ቢያጠፉለትም፣ ለህይወቱ አስጊ የሆነ ጉዳት ስለደረሰበት ብዙም ሳይቆይ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ሊያፍ ችሏል።
ቡሽኔል ራሱን በእሳት እየለኮሰ በነበረበት ሰአት"ነጻነት ለፍልስጤም" በማለት ሲጮህ ተደምጧል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ 250 ሰዎችን ካገተ እና 1200 የሚሆኑትን ደግሞ ከገደለ በኋላ በእስራኤል እና ሀማስ መካከል ከባድ ግጭት ተቀስቅሷል።
እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ባለው የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት እስካሁን ከ30ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ገልጸዋል።