እስራኤል በጋዛ ለስድስት ሳምንት ተኩስ ለማቆም መስማማቷን የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ
በረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ዙሪያ የሃማስ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ተብሏል
እስራኤልና ሃማስ በጋዛ ከረመዳን ጾም በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዛሬ በካይሮ ዳግም ድርድር ይጀምራሉ
እስራኤል በጋዛ ተኩስ ለማቆም እና የታጋችና እስረኛ ልውውጥ ለማድረግ በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ላይ መስማማቷን የአሜሪካ ባለስልጣን ተናገሩ።
ረቂቅ ሰነዱ እስራኤል በጋዛ ለስድስት ሳምንት ተኩስ እንድታቆምና ሃማስም አዛውንቶች፣ ሴቶች እና ህጻናት ታጋቾችን የሚለቅበትን ሂደት የሚያመላክት ነው።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የአሜሪካ ባለስልጣንም “እስራኤል ከሞላ ጎደል ረቂቁን ተቀብላዋለች፤ አሁን ውሳኔው የሃማስ ነው” ማለታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ዘግቧል።
እስራኤልም ሆነች ሃማስ በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን አስተያየት አልሰጡም።
ሁለቱ ወገኖች ዛሬ በግብጽ መዲና በሚጀምሩት ድርድር ከስምምነት ይደርሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተዘገበ ነው።
የግብጽ፣ ኳታር እና አሜሪካ አደራዳሪዎች በጋዛ የሙስሊሞች የረመዳን ጾም ከመጀመሩ በፊት በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ባለፉት ሳምንታት በካይሮ፣ ዶሃ እና ፓሪስ የእስራኤልና ሃማስ ተደራዳሪዎችን ሲያነጋግሩ ቆይተዋል።
በዛሬው የካይሮ ምክክርም ለአዲሱ ረቂቅ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል ብለዋል የግብጽ ባለስልጣናት።
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ እርዳታ ለመቀበል በተሰባሰቡ ፍልስጤማውያን ላይ ተኩስ ከፍታ 118 ሰዎች መገደላቸውን ተከትሎ አለማቀፍ ጫናው በርትቶባታል።
እርዳታ በሚጠባበቁ ፍልስጤማውያን ላይ “ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ” የለም በሚል የምታስተባብለው ቴል አቪቭ፥ ጫናው ቢበዛም ጊዜያዊ ተኩስ አቁም እንጂ ጦሯን ከጋዛ እንድታስወጣ የሚያደርግ ስምምነት ላይ እንደማትደርስ አስታውቃለች።
በእስራኤል የአየር ድብደባ የሞቱ ታጋቾች ቁጥር 70 ደርሷል ያለው ሃማስ በበኩሉ እስራኤል ከጋዛ ለቃ የምትወጣበት መደላድል ካልተፈጠረ ጦርነቱ ቀጣይ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱን ሬውተርስ አስታውሷል።
የጋዛ የጤና ሚኒስቴር 149ኛ ቀኑን በያዘው ጦርነት 30 ሺህ 320 ፍልስጤማውያን ህይወታቸው ማለፉንና ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጿል።
የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማትም በፍጥነት ተኩስ ቆሞ ሰብአዊ ድጋፍ ማቅረብ ካልተቻለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማስጠንቀቃቸውን ቀጥለዋል።