በጋዛ የሞቱ ንጹሀን ቁጥር በይፋ ከተገለጸው በ41 በመቶ ሊጨምር እንደሚችል ጥናተ አመላከተ
ከጥቅምት 2023 እስከ ሰኔ 2024 ድረስ ባሉት ጊዜያት 64 ሺህ ንጹሀን ሞተዋል ብሏል ጥናቱ
ከሟቾቹ መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ፣ ህጻናት እነማ አረጋውን መሆናቸው ተጠቁሟል
በእስራል በጋዛ ከሃማስ ታጣቂዎች ጋር ባካሄደችው ጦርነት የሞቱ ንጹሀን ቁጥር በይፋ ከተገለጸው አኃዝ ሰፊ ልዩነት ሊኖረው እንደሚችል የለንደን የንጽህና እና የትሮፒካል ሕክምና ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት አመላክቷል፡፡
በላንሴት ሜዲካል ጆርናል ሀሙስ ዕለት የታተመው የጥናት ውጤት ከሟቾቹ መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች፣ ህጻናት ወይም አረጋውያን ናቸው ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከህዳር 2023 እስከ ነሀሴ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ባስጠናው ጥናት በዚህ ጊዜ ውስጥ ከተመዘገበው የሟቾች ቁጥር 44 በመቶ ህጻናት እና 26 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ደምድሟል።
የለንደን የንጽህና እና የትሮፒካል ሕክምና ተመራማሪዎች ያደረጉት ጥናት ከጥቅምት 2023 - ሰኔ 2024 ድረስ በጋዛ በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ከ64 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መሞታቸውን ጠቁሟል፡፡
የሀማስ ታጣቂዎችን ሞት በሪፖርቱ ውስጥ ያልተካተተ ሲሆን በነዚህ ጊዜ ውስጥ በሃማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አውጥቶት የነበረው የሟቾች ቁጥር 37,877 ነው፤ ይህም የሟቾችን ቁጥር በ41 በመቶ አሳንሶ ያቀረበ ስለመሆኑ ነው የተነገረው፡፡
ተመራማሪዎቹ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ ሶስት አይነት የመረጃ አሰባሰብ ሳይንሳዊ ቴክኒኮችን መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡
በጥናታቸው ከተመዘገቡት ሞቶች ባለፈ በፍርስራሾች ውስጥ የሚገኙ እና የገቡበት የማይታወቁ እንደሞቱ የተደመደመ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መኖራቸውን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡
ሪፖርቱ ከጦርነቱ ጋር በተገናኘ በቀጥታ የሞቱ ሰዎችን ብቻ ነው ያካተተው ይህ ማለት ፣ በአየር ወይም በተለያዩ የምድር ላይ ጥቃቶች በደረሰባቸው ጉዳት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ብቻ መዝግቢያለሁ ነው ያለው ጥናቱ፡፡
በመሆኑም የጤና አገልግሎት አለማግኘት፣ የልብ ድካም፣ በተላላፊ በሽታዎች፣ የእናቶችን እንክብካቤ እጥረት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች በአግባቡ መውለድ ባለመቻላቸው እና ተያያዥ ምክንያቶች የሞቱ ሰዎች አልተጨመሩም፤ በዚህ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢካተት የሟቾች ቁጥር ከፍ ሊል ይችላል ብሏል ጥናቱ።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር 14 ወራትን በተሻገረው ጦርነት እስካሁን የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ46 ሺህ መሻገሩን በወቅታዊ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡