አሜሪካ ለእስራኤል የ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ማቀዷ ተገለጸ
ዋሽንግተን በ10 ሺዎች የተገደሉበትን ጦርነት እያካሄደች ላለችው የመካከለኛው ምስራቅ አጋሯ እስራኤል ድጋፍ ማድረጓን እንደቀጠለች ነው
የባይደን አስተዳደር እስራኤል የሚደግፈው በኢራን ከሚደገፉት የሀማስ፣ ሄዝቦላ እና ሀውቲ ታጣቂዎች ራሷን እንድትከላከል መሆኑን ይገልጻል
አሜሪካ ለእስራኤል የ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ማቀዷ ተገለጸ።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር ለእስራኤል የ 8 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የጦር መሳሪያ ለመሸጥ ለኮንግረሱ ሀሳብ ማቅረቡን ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናት መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ዋሽንግተን በ10 ሺዎች የተገደሉበትን ጦርነት እያካሄደች ላለችው የመካከለኛው ምስራቅ አጋሯ እስራኤል ድጋፍ ማድረጓን እንደቀጠለች ነው።
በተወካዮች ምክርቤት እና በሴኔቱ መጽደቅ የሚጠበቅበት ይህ የሽያጭ ማዕቀፍ ለተዋጊ ጄቶች የሚሆን ተተኳሽ፣ ተዋጊ ሄሊኮፕተሮቸን እንዲሁም ለከባድ መሳሪያ የሚሆኑ ተተኳሾችን እንደሚናካትት ዘገባው ጠቅሷል።
እንደዘገባው ከሆነ የሽያጭ ማዕቀፉ አነስተኛ ዲያሜትር ያላቸውን ቦሞቦች እና አረሮችንም ያካትታል።
ባይደን እስራኤል አለምአቀፍ ህግን ባከበረ መልኩ ራሷን መከላከል አለባት ብለው እንደሚያምኑ እና አሜሪካ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል መናገራቸውን ሮይተርስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
አሜሪካ በእስራኤል ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንድትጥል ለበርካታ ወራት ተቃውሞዎች ቢካሄዱም አሜሪካ ፖሊሲዋን አልቀየረችም። ባለፈው ነሐሴ ወር አሜሪካ ለእስራኤል የ20 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ወታደራዊ ቁሳቁሶች ማጽደቋ ይታወሳል።
የባይደን አስተዳደር እስራኤል በኢራን ከሚደገፉት የሀማስ፣ ሄዝቦላ እና ሀውቲ ታጣቂዎች ራሷን እንድትከላከል እየረዳት መሆኑን ይገልጻል።
ዋሽንግተን አለምአቀፍ ትችት ቢያጋጥማትም፣ እስራኤል 2.3 ሚሊዮን ህዝብ ያፈናቀለውን የጋዛ ጦርነት ባካሄደችበት ወቀት ከጎኗ ቆማለች። እስራኤል በጋዛ ጦርነት በዘር ማጥፋት ተወንጅላለድ። እስራኤል ይህን ክስ ታስተባብላለች።
የዲሞክራቱ ባይደን ከቢሮ ሊወጡ የቀራቸው ጥቂት ቀናት ሲሆን የሪፐብሊኩ ትራምፕ ወደ ኃይትሀውስ ይገባሉ። ሁለቱም የእስራኤል ጠንካራ ደጋፊዎች መሆናቸው ይታወቃል።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ እስራኤል በጋዛ በፈጸችው መጠነሰፊ ጥቃት የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ 45 ሺ በላይ አልፏል።
ሀማስ ጥቅምት 7፣2023 በጀመረው ጥቃት የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም የተደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጦረቶች እስካሁን አልተሳኩም። የእስራኤል ቀዳሚ አጋርና የጦር መሳሪያ አቅራቢያ የሆነችው ዋሽንግተን ቀደምሲል በጸጥታው ምክርቤት በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የቀረበውን ምክረሀሳብ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ወይም የቬቶ መብቷን በማድረግ ውድቅ አድርጋለች።