በእስራኤል ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 413 ደረሰ
ግብጽ፣ ቱርክ፣ ቻይና እና ሩሲያ ጨምሮ በርካታ ሀገራት በጋዛ የተፈጸመውን ጥቃት አውግዘዋል

የእስራኤል ጦር ግን ሃማስ በተኩስ አቁም ምክረሃሳቡ ላይ ካልተስማማ ጥቃቱ እንደሚቀጥል ዝቷል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ድብደባ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር ከ400 መሻገሩ ተገለጸ።
የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር በዋትስአፕ ገጹ ባጋራው መረጃ የሟቾቹ ቁጥር 413 መድረሱን ጠቁሟል።
ከሁለት ወራቱ የተኩስ አቁም ስምምነት በኋላ የተፈጸመው መጠነሰፊ የአየር ጥቃት ከ560 በላይ ሰዎችን ማቁሰሉንና በርካታ ሰዎችም አሁንም ድረስ በፍርስራሽ ውስጥ እንደሚገኙም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሃማስ ባወጣው መግለጫ "ኔታንያሁ እና ጽንፈኛ መንግስቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመጣስ መወሰኑ በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን እጣፈንታ ጥያቄ ውስጥ ከቷል" ብሏል።
የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል ሪሽቅም የእስራኤል የቦምብ ድብደባ በታጋቾች ላይ "የሞት ፍርድ" እንደማሳለፍ ይቆጠራል ማለታቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽህፈት ቤት ግን ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘምና ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የእስራኤል ጦር የተጠናከረ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ መታዘዙን ነው ያመላከተው።
ሀገራት እስራኤል በጋዛ ስለፈጸመችው የአየር ጥቃት ምን አሉ?
አሜሪካ
የዋይትሃውስ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት እስራኤል በጥቃቱ ዙሪያ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር መምከሯን ተናግረዋል።
"ሃማስ፣ ሃውቲ፣ ኢራን እና ማንኛውም እስራኤል እና አሜሪካን ለማሸበር የሚሞክር ሃይል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋግመው ግልጽ አድርገዋል፤ የገሃነም በሮች በሰፊው ይከፈትላቸዋል" ሲሉም በጋዛ ለተፈጸመው ጥቃት ዋሽንግተን ድጋፍ መስጠቷን አመላክተዋል።
ቻይና
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ቤጂንግ በጋዛ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት "እጅግ ያሳስባታል" ብለዋል። ተፋላሚ ሃይሎች ጋዛን ዳግም ወደ ጦርነት ሊከት የሚችልና ሰፊ የሰብአዊ ቀውስ ከሚፈጥር ድርጊት እንዲቆጠቡም ነው የጠየቁት።
ሩሲያ
ክሬምሊን እስራኤል ከ200 በላይ የአየር ጥቃቶችን በአንድ ቀን መፈጸሟ ጋዛን ዳግም ውጥረት ውስጥ የሚከት ነው ብሏል።
"ንጹሃን በብዛት መሞታቸውን የሚያመላክቱ ዘገባዎች እየወጡ ነው፤ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው፤ ውጥረቱ ጋብ ብሎ (እስራኤልና ሃማስ) ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲመለሱ እንፈልጋለን" ብለዋል የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ።
ግብጽ
ከኳታር እና አሜሪካ ጋር በመሆን እስራኤልና ሃማስን ስታደራድር የቆየችው ግብጽ የእስራኤል የአየር ጥቃት የተኩስ አቁም ስምምነቱን የጣሰ ነው በሚል ተቃውማለች።
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጥቃቱ በመካከለኛው ምስራቅ ዳግም ውጥረት የሚቀሰቅስ መሆኑን ጠቅሷል።
ቱርክ
እስራኤል በጋዛ ለ15 ወራት ያካሄደችውን ጦርነት በተደጋጋሚ ስትቃወም የቆየችው ቱርክ "አዲሱ ጥቃት በፍልስጤማውያን ላይ የተያዘው የዘር ፍጅት ፖሊሲ አካል" ነው ብላለች።
እስራኤል በቀጠናው "አዲስ የግጭት ኡደት" ውስጥ መግባቷ ተቀባይነት እንደሌለው ያነሳው የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፥ የቴል አቪቭ "የጥላቻ ፖሊሲ" የመካከለኛው ምስራቅን መጻኢ ስጋት ውስጥ ከቷል ሲልም ወቅሷል።
ኖርዌይ፣ ኔዘርላንድስ እና ስዊዘርላንድ ባወጡት መግለጫ ጥቃቱን አውግዘው እስራኤልና ሃማስ በፍጥነት ወደ ተኩስ አቁም ድርድር እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
የታጋቾች ቤተሰቦች
በጋዛ የታገቱ እና የጠፉ ቤተሰቦች ፎረም የእስራኤል መንግስት በጋዛ ጥቃት ለመፈጸም መወሰኑ "ታጋቾቹን ለመተው መምረጡን ያሳያል" ብሏል። የእስራኤል መንግስት ታጋቾቹ የሚለቀቁበትን ሁኔታ ከሚያመቻቸው የተኩስ አቁም ስምምነት ይልቅ የአየር ጥቃትን መምረጡ እንዳሳዘነውም በመጥቀስ።
የየመኑ ሃውቲ
በአሜሪካ ተከታታይ የአየር ጥቃት እየተፈጸመበት የሚገኘው ሃውቲ እስከመጨረሻው ጠብታ ለፍልስጤማውያን ድጋፉን እንደሚሰጥ ገልጿል።
"ጽዮናውያን በጋዛ ዳግም የጀመሩትን ወረራ እናወግዛለን፤ የፍልስጤም ህዝብ በአውደ ውጊያው ብቻውን አይሆንም፤ የመን ከጎናቸው ሆና ድጋፏን ትቀጥላለች" ብሏል ቡድኑ ባወጣው መግለጫ።