እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ የአየር ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ተገደሉ
ሃማስ፥ እስራኤል የጀመረችው ድብደባ በታጋቾች ላይ "የሞት ፍርድ" እንደማሳለፍ ይቆጠራል ብሏል

ኔታንያሁ የተኩስ አቁም ማራዘሚያውን ባልተቀበለው ሃማስ ላይ የተጠናከረ እርምጃ እንዲወሰድ አዘዋል
እስራኤል በጋዛ ከሁለት ወራት ወዲህ ከፍተኛውን የቦምብ ጥቃት ፈጽማ በጥቂቱ የ330 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነገረ።
የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ ክፍል ከ200 በላይ የአየር ጥቃቶች ፈጽሟል።
በጥቃቶቹ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ ከ50 በላይ ህጻናት እና 28 ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።
የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩባቸው ድንኳኖች እና ቤቶች ላይ ኢላማ ያደረጉት ጥቃቶች ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ ከ250 በላይ ሰዎችን ማቁሰላቸውም ነው የጠቆመው።
የእስራኤል ጦር እና የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋሙ "ሺን ቤት" በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት በሃማስ ይዞታዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት መክፈታቸውን ጠቁመዋል።
ኔታንያሁ ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለማራዘምና ታጋቾችን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆኑ የእስራኤል ጦር የአየር ጥቃት እንዲፈጽም አዘዋል፤ በቀጣይም የምድር ውጊያ ሊጀመር ይችላል ተብሏል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝም ሃማስ ታጋቾችን የማይለቅ ከሆነ በጋዛ የሚወሰደው እርምጃ አድማሱን እያሰፋ እንደሚሄድ ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ በበኩሉ የእስራኤል የቦምብ ድብደባ በታጋቾች ላይ "የሞት ፍርድ" እንደማሳለፍ ይቆጠራል ብሏል።
"የኔታንያሁ ዳግም ጦርነት የመጀመር ውሳኔ ታጋቾችን መስዋዕት የሚያደርጋቸው ነው" ብለዋል የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል ሪሽቅ።
በአሁኑ ወቅት በጋዛ የቀሩት ታጋቾች 59 ሲሆኑ፥ እስራኤል 35ቱ ህይወታቸው ማለፉን ታምናለች።
እስራኤልና ሃማስ ከሁለት ሳምንት በፊት የተጠናቀቀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ ተኩስ አቁም ለ42 ቀናት እንዲያራዝሙ ምክረሃሳብ ያቀረበችው አሜሪካ በጋዛ ዳግም ለተጀመረው የአየር ጥቃት ድጋፍ ሰጥታለች።
የዋይትሃውስ ቃልአቀባይ ካሮሊን ሌቪት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ማብራሪያ "ሃማስ፣ ሃውቲ፣ ኢራን እና ማንኛውም እስራኤል እና አሜሪካን ለማሸበር የሚሞክር ሃይል ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍል ፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋግመው ግልጽ አድርገዋል፤ የገሃነም በሮች በሰፊው ይከፈትላቸዋል" ብለዋል።
እስራኤል ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዳይገባ በማገድ እና የኤሌክትሪክ ሃይል ስርጭትን ሙሉ በሙሉ በማቋረጥ በሃማስ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች።
ይሁን እንጂ ሃማስ በአሜሪካ የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ የቀረበው የተኩስ አቁም ማራዘሚያ እስራኤል ጦሯን ከጋዛ እንድታስወጣ የሚጠይቀውን ሁለተኛ ምዕራፍ ላለመቀበል የተደረገ ነው በሚል ውድቅ እንዳደረገው ይታውሳል።