
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው መጠነሰፊ የአየር ጥቃት ከ330 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው የአየር ጥቃት በርከት ያሉ የሃማስ አመራሮች መገደለቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል።
እስራኤል በጋዛ ከሁለት ወራት ወዲህ ከፍተኛውን የቦምብ ጥቃት ሌሊት መፈጸሟን ተከትሎ ነው የሃማስ አመራሮች የተገደሉት ተብሏል።
ከእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር እና ከፊልስጤም ውስጥ የሚገኙ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሆነ በሌሊቱ ጥቃት 4 ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በርከት ያሉ መካለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የሃማስ አመራሮች ተገድለዋል።
በእስራኤል ጥቃት ከተገደሉ አመራሮች መካከልም፤
አቡ ኦቤዲያ አል-ጃማሲ- የሃማስ ፖለቲካ ቢሮ አባልና የአደጋ ጊዜ ኮሚቴ ኃላፊ
ብርጋዴር ጄነራል ባህጃት ሃሰን አቡ ሱልጣን- በጋዛ የውስጥ ኦፕሬሽኖች ኃላፊ
ኢሳም አል-ዳሊስ- የሃማስ ፖለቲካ ቢሮ ኃላፊ
ማህሙድ አቡ-ዋትፋ- ከሃማስ ጋር ግንኙነት ያለው ምክትል የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር
እንዲሁም በእስራኤል መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት በሃማስ ውስጥ መካከለኛ ወታደራዊ እና የፖለቲካ መሪዎችም መገደላቸውን የእስራኤል ካን ቻናል ዘገባ ያመለክታል።
ከአመራሮቹ በተጨማሪም እስራኤል በጋዛ ከሁለት ወራት ወዲህ ከፍተኛውን የቦምብ ጥቃት ፈጽማ በጥቂቱ የ330 ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።
በጥቃቶቹ ህይወታቸው ካለፈው ውስጥ ከ50 በላይ ህጻናት እና 28 ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።
የእስራኤል ጦር እና የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋሙ "ሺን ቤት" በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት በሃማስ ይዞታዎች ላይ መጠነሰፊ ጥቃት መክፈታቸውን ጠቁመዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ በበኩሉ የእስራኤል የቦምብ ድብደባ በታጋቾች ላይ "የሞት ፍርድ" እንደማሳለፍ ይቆጠራል ብሏል።
"የኔታንያሁ ዳግም ጦርነት የመጀመር ውሳኔ ታጋቾችን መስዋዕት የሚያደርጋቸው ነው" ብለዋል የቡድኑ የፖለቲካ ቢሮ አባል ኢዛት አል ሪሽቅ።