ኒው ደልሂን ያስጨነቀው 72 ሜትር የሚረዝመው የአለማችን ትልቁ የቆሻሻ ክምር
50 የእግር ኳስ ሜዳዎችን የሚሸፈነው ክምር 14 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ቆሻሻን ይዟል

በዚህ ስፍራ አቅራቢያ ኑሯቸውን የመሰረቱ ህንዳውን ለልብ እና ለመተንፈሻ አካላት በሽታዎች ተጋላጭ መሆናቸው ተነግሯል
በህንድ ኒው ደልሂ የሚገኘው የጋዚፑር የቆሻሻ ክምር በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋቱ እና ከፍታው ቀዳሚ ነው፡፡
በ1984 በምስራቃዊ ደልሂ የተቋቋመው የቆሻሻ መጣያ ስፍራ በአመታት ውስጥ ወደ ተራራነት የተለወጠ ሲሆን በፈረንጆቹ 2002 ማስተናገድ ከሚችለው አቅም በላይ ደርሶ ነበር፡፡
ሆኖም ስፍራው አሁንም በየቀኑ በመቶ ቶን የሚመመዘን ቆሻሻ ከመላው ደልሂ ተጠራቅሞ ይደፋበታል በአሁኑ ወቅትም 14 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በስፍራው እንደሚገኝ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡
70 ሄክታር ወይም 50 የእግር ኳስ ሜዳዎች ስፍራ ላይ ያረፈው የቆሻሻ ክምር ታዋቂውን የታጅማሀል ህንጻ ወይም 72 ሜትር እርዝመት አለው፡፡
34 .6 ሚሊየን ህዝብ በሚኖርባት ኒው ደልሂ የሚገኘው የጋዚፑር የቆሻሻ ክምር በአቅራቢያው የሚኖሩ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎችን ኑሮ ፈታኝ አድርጓል፡፡
ከስፍራው የሚነሳው መጥፎ ጠረን በተለይ በበጋ ወቅቶች ጠንከር የሚል በመሆኑ ለብዙዎች የጤና ጠንክ ሆኗል፤ አልፎ አልፎ የሚቃጣጠለውን እሳት ተከትሎ ወደ አየር የሚለቀቀው መርዛማ ጭስም ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት በስፍራው ያጋጠመው የቆሻሻ ክምር ናዳ በርካታ ተሸከርካሪዎች እና ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከነዚህ መካከል እ.ኤ.አ. በመስከረም 2017 ከ50 ሚሊዮን ቶን በላይ ቆሻሻ ተንዶ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች የሞቱበት አደጋ ይጠቀሳል፡፡
በተጨማሪም በነሀሴ 2024 በቆሻሻ ማጠራቀሚያው ላይ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ በአካባቢው ከፍተኛ የጤና እና የመተንፈስ ችግር የፈጠረ ደልሂን በጭስ ያፈነ አደጋም አጋጥሞ ነበር፡፡
ስካይ ኒውስ ያነጋገራቸው በስፍራው ከ50 አመት በላይ የኖሩ የ71 አመት ግለሰብ መንግስታት ለዚህ ችግር መፍትሄ እንደሚሰጡ በተደጋጋሚ ቃል ቢገቡም እስካሁን መፍትሄ አለማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህ የተነሳም በቆሻሻ ክምሩ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች በስፋት ለልብ እና ለመተንፈሻ አካላት የጤና ችግር ተጋላጭ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በየቀኑ 11 ሺህ ቶን ቆሻሻ በምታመርተው ኒው ደልሂ ባለስልጣናት አማራጭ የቆሻሻ ማስወገጂያ መንገዶችን ለማስተዋወቅ ጥናት እያስጠኑ ይገኛሉ