ሊዮኔል ሜሲ በገጠመው ጉዳት ከአለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ውጭ ሆነ
ሜሲ አርጀንቲና ከኡራጓይ እና ብራዚል ጋር ለምታካሂደው የማጣሪያ ጨዋታ እንደማይደርስ ክለቡ ኢንተር ሚያሚ አስታውቋል

አርጀንቲና የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ምድብን በአምስት ነጥብ ልዩነት እየመራች ነው
ሊዮኔል ሜሲ በገጠመው ጉዳት አርጀንቲና በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከኡራጓይ እና ብራዚል ጋር በምታደርገው ጨዋታ እንደማይሰለፍ ተገለጸ።
ሜሲ ኢንተር ሚያሚ አትላንታን ባሸነፈበት ጨዋታ የብሽሽት ጉዳት እንዳጋጠመው የምርመራ ውጤቱ ማሳየቱን ክለቡ አስታውቋል።
በዚህም የፊታችን አርብ በሞንቴቪዲዮ ከኡራጋይ ጋር የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የሚያደርገው የአርጀንቲና ብሄራዊ ቡድንን አይቀላቀልም።
ጉዳቱ በቀጣይ ሳምንት ከብራዚል ጋር በሚካሄደው የማጣሪያ ጨዋታ እንዳይሰለፍ ያግደዋልም ነው የተባለው።
እነዚህ ሁለት ጨዋታዎች የ2022ቱ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮን አርጀንቲና በ2026ቱ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ለማረጋገጥ ያስችሏታል።
አርጀንቲና 10 ሀገራትን ባካታተው የደቡብ አሜሪካ የማጥሪያ ምድብ በ25 ነጥብ እየመራች ነው። ኡራጓይ በ20፣ ኢኳዶር እና ኮሎምቢያ በእኩል 19 ነጥብ ይከተላሉ።
ከምድቡ እስከ ስድስተኛ የሚያጠናቅቁ ሀገራት አሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ በጋራ በሚያዘጋጁት የአለም ዋንጫ ይሳተፋሉ። በአሁኑ ወቅት ሰባተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቦሊቪያ ናት።
እስካሁን በተደረጉ 12 የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ሜሲ ስድስት ፎሎችን በማስቆጠር የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢነትን ይመራል።
አርጀንቲና ከሜሲ ባሻገር የሮማውን አጥቂ ፓውሎ ዲያባላ እና የሪቨር ፕሌቱን ተከላካይ ፓውሎ ሞንቴል በጉዳት ማጣቷን ሱፐርስፖርት አስነብቧል።
ከአርጀንቲና በሰባት ነጥብ ዝቅ ብላ አምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ብራዚልም ከአርጀንቲና ጋር በምታደርገው ጨዋታ የ33 አመቱን አጥቂ ኔይማር እንዳማታሰልፍ ተገልጿል። ኔይማር በጭኑ ላይ የገጠመው ጉዳት ብሄራዊ ቡድኑን የሚቀላቀልበትን ጊዜ እንዲያራዝም አድርጎታል ተብሏል።