በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 26ሺ ደረሰ
እስራኤል በጋዛ የዘርማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚል ክስ በደቡብ አፍሪካ ተከፍቶባት በአለምአቀፉ ፍርድ ቤት ቀርባ እየተከላከለች ነው
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በጋዛ የተደገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 26ሺ መድረሱን የጋዛ ጤና ሚኒስቴርን አስታውቋል
በጋዛ የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 26ሺ ደረሰ።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በጋዛ የተደገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 26ሺ መድረሱን ሮይተርስ የጋዛ ጤና ሚኒስቴርን ጠቅሶ ዘግቧል።
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ጦርነቱ ከተጀመረበት ከባለፈው አመት ጥቅምት ወር ወዲህ 26,083 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን 64,487 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል አደጋ አጋጥሟቸዋል ብሏል።
ሚኒስቴሩ ባወጣው ሪፖርት ንጹሃን እና ታጣቂዎችን በሚል ለይቶ ያላስቀመጠው ቢሆንም፣ ከተገደሉት ውስጥ 2/3ኛ የሚሆኑት ህጻናት እና ሴቶች ናቸው ብሏል።
የጤና ሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አሽራፍ አል ቂድራ ባለፉት 24 ሰአታት ውስጥ 183 ሰዎች መገደላቸውን እና 377 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን አስታውቀዋል።
አራት ወራትን ባስቆጠረው ጦርነት፣ እስራኤል ባካሄደችው ከባድ ጥቃት ሰፊ የጋዛ ቦታን ወደ ባዶነት ቀይራዋለች።
የእስራኤል እና ሀማስ ጦርነት የተጀመረው፣ ሀማስ በ50 አመታት ወስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ድንበር በመጣሰ 1200 ሰዎችን ገድሎ እና 240 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነው።
ይህን ተከትሎ እስራኤል በሀማስ ላይ ጦርነት ማወጇ ይታወሳል።
እስራእል በጋዛ እያደረሰችው ባለው ሁሉን አቀፍ ጥቃት የጋዛ ነዋራዎች ለከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ተመድ በተደጋጋሚ ገልጿል።
ጦርነቱ እንዲቆም እና በቂ የሰብአዊ እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ አለምአቀፍ ጫና ቢደረግም፣ ሀማስን ከምድረገጽ አጠፋለሁ የምትለው እስራኤል እና አጋሯ አሜሪካ ተኩስ እንዲቆም አይፈልጉም።
እስራኤል በጋዛ የዘርማጥፋት ወንጀል ፈጽማለች የሚል ክስ በደቡብ አፍሪካ ተከፍቶባት በአለምአቀፉ ፍርድ ቤት ቀርባ እየተከላከለች ነው።
ደቡብ አፍሪካ ጉዳዩን እያየ ያለው ፍርድ ቤት በቅድሚያ ጦርነቱን እንዲያስቆምላት ጠይቃ ነበር።
ፍርድቤቱ እስራኤል የዘርማጥፋት ድርጊቶችን እንዳትፈጽም ትዕዛዝ አስተላልፏል፤ ነገርግን ተኩስ እንዲቆም ውሳኔ ሳያሳልፍ ቀርቷል።