እስራኤል በጋዛ በ24 ስአት ውስጥ 24 ወታደሮቼ ተገድለዋል አለች
ይህም ቴል አቪቭ በጋዛ የእግረኛ ጦሯን ካስገባች ወዲህ በአንድ ቀን በርካታ ወታደሮቿን ያጣችበት ሆኖ ተመዝግቧል
እስራኤል ከሶስት ወራት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት ከ200 በላይ ወታደሮቿ መገደላቸውን ገልጻለች
የእስራኤል ጦር ባለፉት 24 ስአታት ውስጥ 24 የሀገሪቱ ወታደሮች መገደላቸውን አስታውቋል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳኔል ሃጋሪ እንደገለጹት፥ 21ዱ ወታደሮች የተገደሉት በማዕከላዊ ጋዛ ኪሱፉም በተባለ አካባቢ ነው።
የሃማስ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ ሁለት ህንጻዎች ላይ ፈንጂ ሲያጠምዱ የነበሩት ወታደሮች ቦምብ ተወርውሮባቸው ህይወታቸው ማለፉንም ነው ቃል አቀባዩ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
ፈንጂ የተጠመደባቸው ህንጻዎች ተደርምሰው ወታደሮቹ ላይ ማረፋቸውንም አብራርተዋል።
የእስራኤል ጦር የ21 ወታደሮቹን ህይወት የቀጠፈውን አደጋ በዝርዝር እንደሚመረምርም ገልጿል።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢሳቅ ሄርዞግ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ የወታደሮቹ ህልፈት “ትግስትን የሚፈታተን ከባድ ጠዋት” እንድናሳልፍ አስገድዷል ብለዋል።
በፍንዳታው ህይወታቸው ካለፈው 21 ወታደሮች ባሻገር በደቡባዊ ጋዛ ሶስት የእስራኤል ወታደሮች መገደላቸው መገለጹንም ሬውተርስ ዘግቧል።
በ24 ስአት ውስጥ የተመዘገበው የወታደሮች ሞት መጠን እስራኤል ወደ ጋዛ ከገባች ወዲህ ከፍተኛው ነው ተብሏል።
የትናንቱ አሃዝ እስራኤል ከሶስት ወራት በላይ ባስቆጠረው ጦርነት የተገደሉባትን ወታደሮች ቁጥር 208 ያደርሰዋል።
እስራኤል የሃማስ ዋነኛ ማዕከል ናት ያለቻት ካን ዩኒስ ላይ ትኩረት በማድረግ የምትፈጽመው ድብደባ መቀጠሉ ተገልጿል።
አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራትና አለማቀፍ ተቋማት ቴል አቪቭ እየወሰደችው ያለው እርምጃ ንጹሃንን መጠበቅ እንዳለበት እያሳሰቡ ነው።
ይሁን እንጂ ሆስፒታሎችን ጭምር ኢላማ ባደረጉ የእስራኤል የምድር እና አየር ጥቃቶች የተገደሉ ፍልስጤማውያን ቁጥር 25 ሺህ 295 መድረሱን ነው የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር መግለጫ የሚያሳየው።