የእስራኤል 'ቱ ስቴት ሶሉሽን'ን መቃወም ተቀባይነት የለውም- ተመድ
ፍልስጤማውያን ዌስትባንክን፣ ምስራቅ እየሩሳሌምን እና ጋዛ ስርጥን እና በ1967 በእስራኤል የተያዙ ግዛቶችን ያካተተ ሀገር መመስረት ይፈልጋሉ
ጉተሬዝ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ በተካሄደ ከፍተኛ የጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ላይ "የእስራኤል ወረራ ማብቃረት አለበት" ብለዋል
ተመድ እስራኤል 'ቱ ስቴት ሶሉሽን'ን መቃወም ተቀባይነት የለውም አለ።
የተመድ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የእስራኤል 'ቱ ስቴት ሶሉሽን'ን መቃወም ተቀባይነት የሌለው እና ለአክራሪዎች የልብልብ የሚሰጥ ሲሉ ተናግረዋል።
ጉተሬዝ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ በተካሄደ ከፍተኛ የጸጥታው ምክርቤት ስብሰባ ላይ "የእስራኤል ወረራ ማብቃረት አለበት" ብለዋል።
15 አባላት ያሉት የጸጥታው ምክርቤት ከእስራኤል ሀገር ጎን ለጎን የሚታወቅ ድንበር ያለው የፍልስጤም ሀገር እንዲመሰረት ካጸደቀ ቆይቷል። ፍልስጤማውያን ዌስትባንክን፣ ምስራቅ እየሩሳሌምን እና ጋዛ ስርጥን እና በ1967 በእስራኤል የተያዙ ግዛቶችን ያካተተ ሀገር መመስረት ይፈልጋሉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያማን ኒታንያሁ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት እስራኤል የፍልስጤም ግዛቶችን ጨምሮ ከጆርዳን ወንዝ በስተምዕራብ ያሉ ቦታዎችን ጸጥታ ሁኔታ መቆጣጠር ትፈልጋለች።
ኔታንያሁ እክለውም ይህ "ከሉአላዊነት መርህ ጋር ሊጋጭ ይችላል፤ ግን ምን ማድረግ እንችላለን" ሲሉ ተናግረዋል።
ሀማስ ባለፈው አመት ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።
እንደጋዛ የጤና ባለስልጣናት ከሆነ እስራኤል በጋዛ ላይ እየወሰደች ባለው የእግረኛ ጦር እና የአየር ጥቃት የሞቱ ፍልስጤማውን ቁጥር 25ሺ ደርሷል።
ጉተሬዝ ጋዛ እየወደመች ያለበት መጠን እና ፍጥነት በቅርብ ታሪክ ውስጥ ያልታየ ነው ብለዋል።
"የፍልስጤማውያን ጠቅላላ ጥቃት ምንም ምክንያታዊ ሊያደርግ የሚችል የለም"
የፍስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪያድ አልማሊኪ "ኔታንያሁ የፖለቲካ ስልጣናቸውን በሚሊዮን ፍልጤማውያን ኪሳራ ለማስቀጠል" የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ በጸጥታው ምክርቤት ጉባኤ ላይ ከሰዋቸዋል።
የእስራኤል አጋር የሆነችው አሜሪካ በጸጥታው ምክርቤት የሚቀርቡ የውሳኔ ሀሳቦች ከእስራኤል ፍላጎት ጋር ካልተጣጣሙ እንዳይጸድቁ ታደርጋለች።