የጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት በዚህ ሳምንት ሊፈጸም እንደሚችል አሜሪካ አስታወቀች
ተደራዳሪዎች የድርድሩን የመጨረሻ ሂደት ለማጠናቀቅ በዛሬው ዕለት በኳታር ዶሀ ይገናኛሉ
እስራኤል እና ሀማስ ከእስከዛሬው በተለየ ሁኔታ ስምምነቱ ለውጤት መቃረቡን አረጋግጠዋል
ለ15 ወራት የዘለቀውን የሀማስ እስራኤል ጦርነት ለማስቆም የሚደረገው ድርድር በዚህ ሳምንት ለስምምነት ሊበቃ እንደሚችል አሜሪካ ገለጸች፡፡
የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጄክ ሱሊቫን “ለስምምነት ተቃርበናል፤ በዚህ ሳምንት ስምምነቱ መቋጫ ያገኛል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
አክለውም ባለፈው ሰኔ ወር በተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የቀረበው የስምምነት ሀሳብ በጋዛ የተኩስ ማቆም እና ታጋቾችን ማስለቀቅ ያካትታል ብለዋል፡፡
ባይደን በበኩላቸው ለስምምነት የተጠጋው የድርድር ሀሳብ “ታጋቾቹን ነፃ ያወጣል፣ ጦርነቱን ያስቆማል፣ ለእስራኤል የደህንነት ዋስትና ይሰጣል እንዲሁም በዚህ ጦርነት ክፉኛ ለተሰጎዱ ፍልስጤማውያን ሰብዓዊ ዕርዳታ እንድናደርግ ያስችለናል” ብለዋል።
አደራዳሪዎቹ በትላንትነው ዕለት የስምምነቱን ረቂቅ ለሀማስ እና ለእስራኤል መስጠታቸውን የዘገበው ሮይተርስ በኳታር ዶሀ በተደረገው የድርድር ሂደት ላይ የጆ ባይደን እና የትራምፕ መልዕክተኞች መሳተፋቸውን ገልጿል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትረ አንቶኒ ብሊንከን በመጨረሻ የስምምነት ሰነዱ ዙርያ ሁለቱም ወገኖች አዎንታዊ ምላሽ ማሳየታቸውን ገልጸው በዛሬው ዕለት ሀማስ ከድህረ ግጭት በኋላ ጋዛን በተመለከተ ያለውን እቅድ ያቀርባል ብለዋል፡፡
የእስራኤል ባለስልጣነት እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት 98 ታጋቾች በሀማስ እጅ የሚገኙ ሲሆን ስምምነቱ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሀማስ በመጀመሪያው ዙር 33 ታጋቾችችን የሚለቅ ይሆናል፡፡
የእስራኤሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር "ከቀድሞው በጣም በተሻለ ሁኔታ ለስምምነት ቀርበናል፤ በቅርቡ በድርድሩ ዙሪያ መልካም ውጤት ይፋ እንደምናደርግ ተስፋ አለኝ። ይህ እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ አሜሪካውያን ወዳጆቻችንን ላመሰግን እወዳለሁ” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡
ስምምነት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳወቀው ሀማስ በበኩሉ “በአንዳንድ አንኳር ጉዳዮች ላይ የነበሩንን ልዩነቶች አጥብበናል፤ የቀረውን በቅርቡ ለመጨረስ እየሰራን ነው” ብሏል፡፡
ተፋላሚዎቹ ወገኖች ታጋቾች እና እስረኞችን ለማስለቀቅ ግጭቱን ለማስቆም በመርህ ደረጃ በተደጋጋሚ ተስማምተዋል፡፡
ነገር ግን ሃማስ ስምምነቱ ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲያስቆም እና የእስራኤልን ከጋዛ ሙሉ ለሙሉ መውጣት ማካተት አለበት ሲል፤ እስራኤል በበኩሏ ሃማስ ሙሉ ለሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ጦርነቱን እንደማታቆም ትናግራለች።
ሮይተርስ በዘገባው ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባይደን ስልጣን ከመልቀቃቸው በፊት የጋዛውን ጦርነት ማስቆም ከቻሉ እንደትልቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት የሚቆጠር ሲሆን በተመሳሳይ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ጦርነቱን አስቆማለሁ ላሉት ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደ ሰኬት የሚቆጠር ነው ብሏል፡፡