ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሹመትን አጽድቋል
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መሐመድ እድሪስ የሰላም ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሹመትን አጽድቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር እንዲሆኑ በእጩነት አቅርበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ጉባዔ ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሆነው እንዲሾሙ የቀረበለትን ጥያቄ ተመልክቷ።
በዚህ መሰረት ምክር ቤቱ ሹመታቸውም በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ መሐመድ እድሪስ የሰላም ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።
አዲሱ ተሿሚ ከዚህ ቀደም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን መሐመድ እድሪስ ተክተው ይሰራሉ።
ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በአስተማሪነት እና በአመራርነት ማገልገላቸው ተገልጿል።
በዚህም የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ መምህር፣ የኮሚኒኬሽን እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም በዩንቨርስቲው የማርኬቲንግና ኮሚኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን አገልግለዋል።