የሀውቲ አማጺዎች በእስራኤል ላይ በሰነዘሩት ጥቃት 11 ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው
ጉዳቱ የደረሰው ቡድኑ በሰአታት ልዩነት ውስጥ በፈጸመው ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ነው
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር መስርያቤት የጥቃቱ ኢላማ እንደነበር ሀውቲ ባወጣው መግለጫ አሳውቋል
በኢራን የሚደገፉት የየመን የሀውቲ አማፂያን ሰኞ ማምሻውን እና ማክሰኞ ንጋት ላይ በሰአታት ልዩነት ውስጥ ተከታታይ የባለስቲክ ሚሳይሎችን በመተኮስ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ወደ መጠለያ ጣብያ እንዲገቡ አስገድደዋል፡፡
ማክሰኞ ማለዳ ላይ በተፈጸመው ጥቃት በማዕከላዊ እስራኤል 11 ሰዎች ሲጎዱ የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሳይረኖች ዜጎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ድምጽ ሲያሰሙ ተሰምተዋል፡፡
ጉዳት ደርሶባቸዋል የተባሉ ሰዎችም ወደ መጠለያ ጣብያዎች ሲያመሩ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል፡፡
ጦሩ ከጥቃቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ አይዲኤፍ የመጀመሪያውን ሚሳይል በተሳካ ሁኔታ አመሻሽ 12፡30 ላይ ማክሸፉን ይፋ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይ ንጋት ላይ በማዕከላዊ እስራኤል በኩል የደረሰው ጥቃት ቤን ጎሪዮን የተባለውን ኤር ፖርት እንቅስቃሴ ለ20 ደቂቃ ያህል አስተጓግሎ ቆይቷል፡፡
ሚሳይሎችን ለማስወንጨፍ የተተኮሱ መቃወሚያዎች በዌስት ባንክ፣በዮርዳኖስ ሸለቆ፣አፉላ አካባቢ እና በቤቴ ሺአን አቅራቢያ የሚሳኤሎች ስብርባሪ ጉዳት ማድረሱንም ገልጿል፡፡
የየመኑ ሀውቲ በበኩሉ ለጥቃቱ ሃላፊነቱን ወስዶ ኢላማው በእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር መስርያቤት ላይ ያነጣጠረ ነበር ብሏል፡፡
ከዚህ ባለፈም ጃፋ በተባለው የእስራል አየር ሀይል ማዘዣ ላይ በአራት ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) ጥቃት መፈጸሙን ነው የገለጸው፡፡
ሃውቲዎች በመግለጫቸው እስራኤል በጋዛ የከፈተችውን ጦርነት እስካላቆመች ድረስ ከሚሳይል ጥቃቶች በዘለለ በቀይ ባህር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ከአሜሪካ ፣ እስራኤል እና ብሪታንያ ጋር ግንኙነት ባላቸው መርከቦች ላይ የሚያደርሱትን ጥቃት እንደሚቀጥሉ ዝተዋል፡፡
የየመን ዋና ከተማ ሰንአን ተቆጣጥረው የሚገኙት ሀውቲዎች የጋዛው ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በድሮን እና በሚሳኤል የተለያዩ ጥቃቶችን የፈጸሙ ሲሆን እንደ ታይምስ ኦፍ እስራኤል ጋዜጣ ዘገባ ቡድኑ እስካሁን 40 የሚደርሱ ባለስቲክ ሚሳኤሎችን ወደ እስራኤል ተኩሷል፡፡
በምላሹ እስራኤል በዋና ከተማዋ የሀውቲ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ ይዞታዎች ናቸው ባለቻቸው ስፍራዎች ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃት ፈጽማለች፡፡