ሩሲያ የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ቀጠናዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀች
በኢራን ላይ ያነጣጠሩ ጸብ አጫሪ ወቀሳዎችም በእሳት ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ ናቸው ብለዋል የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ
ሩሲያ በጋዛ ግጭት እንዲቆም የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቃለች
ሩሲያ በጋራ የቀጠለው ጦርነት ቀጠናውን ትርምስ ውስጥ የሚከት ነው ስትል አስጠንቅቃለች።
በጦርነቱ ውስጥ ኢራንን የሚወነጅሉ ጸባ አጫሪ ንግግሮችን ማድረግም ግጭቱን ያባብሰዋል ነው ያሉት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት እንዲባባስ የሚፈልግ ሃይል (የሁለቱም አጋር) አለ ብለው እንደማያምኑ ከሰሞኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሩሲያ በጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ጦርነቱ ጋብ እንዲል የሚጠይቀውንና በብራዚል የቀረበውን የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብ “ዘላቂ የተኩስ አቁም” እንዲደረስ የሚጠይቅ ይሁን በሚል ማሻሻያ አቅርባ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
የውሳኔ ሃሳቡ ትናንት ድምጽን በድምጽ የመሻር ስልጣን ባላት አሜሪካ ድምጽ ተነፍጎት ሳይጸድቅ መቅረቱም ይታወሳል።
ሞስኮ በጋዛ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ 193 አባላት ያሉት የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ ተጠርቶ ውሳኔ ላይ ካልተደረሰ የጸጥታው ምክርቤት የውሳኔ ሃሳብ በቀጣይም በዋሽንግተን ውድቅ ሊደረግ ይችላል የሚል ስጋት አላት።
በሃማስ እና እስራኤል ጦርነት የሩሲያ አቋም ምንድን ነው?
ሞስኮ እስራኤል ለሃማስ ጥቃት ምላሽ መስጠትና ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት መግለጫ ያወጣችው ዘግየት ብላ ነው።
ክሬምሊን 16 ሩሲያውያን ጭምር ለተገደሉበት የሃማስ ጥቃት ቴል አቪቭ ምላሽ መስጠቷ ተገቢ ነው ቢልም እስራኤል ከ2 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎች ያሉበትን ጋዛ በአየር መደብደቧን በጽኑ ተቃውሟል።
ፍልስጤም ነጻ ሀገር እንድትሆን የምትደግፈው ሩሲያ እንደ ምዕራባውያን ሀገራት ሃማስን በሽብርተኝነት አልፈረጀችም።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ከእስራኤል ጋር በሶሪያ የተቃረነ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቢኖራቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መስርተዋል።
ፑቲን ከቴል አቪቭ ወዳጅ ሀገር አሜሪካ ጋር የገቡበት ፍጥጫ ግን በጋዛ ወቅታዊ ሁኔታ ኔታንያሁን የማያስደስት ንግግር እንዲያደርጉ እያስገደደ ነው።
የሃማስና እስራኤል ጦርነት ሌላኛው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ክሽፈት ማሳያ ያደረጉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፥ “ከአውዳሚ” አካሄድ ይልቅ መረጋጋትን የሚያሰፍን መፍትሄን መፈለግ ያሻል ብለዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል ሃማስን ትደግፋለች በምትባለው ኢራን ላይ ጣታቸውን ከመቀሰር ይልቅ በጋዛ ሚሊየኖችን ከስቃይ የሚገላግል መፍትሄን እንዲፈልጉም መጠየቃቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭም አሜሪካ በጦርነቱ ኢራንን መውቀሷ ጸብ አጫሪ ድርጊት መሆኑንና በቀጠናው ቀውስ የሚፈጥር መሆኑን ነው ያነሱት።
በተያያዘ በኢራን የሚደገፉ ሃይሎች በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ማድረጋቸው ተነገሯል።
ቴህራን ሃማስ በእስራኤል ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት ሲያደርስ ምንም አይነት ድጋፍ እንዳላደረገች ብትገልጽም የዋሽንግተን ድጋፍ ከቀጠለ ግን ጦርነቱ ቀጠናዊ መልክ መያዙ እንደማይቀር ማስጠንቀቁ ይታወሳል።