አወዛጋቢዋ አልጄሪያዊት ቦክሰኛ በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸነፈች
በጾታዋ ሁኔታ መነጋገርያ ሆነ የሰነበተችው ኢማን ከሊፍ ቻይናዊዋን የአለም ሻምፒዮና አሸንፋ ሜዳልያውን ወስዳለች
የ25 አመቷ ቦክሰኛ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በነበራት ተሳትፎ የብር ሜዳሊያ ማግኝት ችላ ነበር
በዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ በጾታዋ ሁኔታ መነጋገርያ ሆና የቆየችው አልጄርያዊት ቦክሰኛ ኢማን ከሊፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች፡፡
በአምስት ዙር በተደረገው ግጥሚያ ኢማን ከሊፍ በዳኞች ውሳኔ ቻይናዊቷን የአለም ሻምፒዮና ያንግ ሊዩን በማሸነፍ ነው የወርቅ ሜዳልያውን ያጠለቀችው፡፡
በግጥሚያው የበላይነቱን ይዛ የነበረችው አልጄሪያዊት የመጨረሻው ደውል ከተሰማ በኋላ ውጤቱ ከመታወቁ በፊት አሸናፊ ስለመሆኗ እርግጠኛ በመሆን ደስታዋን ስትገልጽ ታይታለች፡፡
ቻይናዊቷ ያንግ እና ኢማን ባሳለፍነው አመት ለአለም ሻምፒዮና ክብር ሊወዳደሩ የነበረ ቢሆንም አለም አቀፉ የቦክስ አሶሴሽን ኢማንን በጾታዋ ምክንያት ከውድድሩ እንድትታገድ አድርጓት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ኢማን ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት በጾታዋ ምክንያት እየደረሰባት የነበረው ጫና በውድድሩ እንድትበረታ እና አሸናፊ እንድትሆን እንዳስቻላት ተናግራለች፡፡
“ከዚህ ቀደም በቶኪዮ በተካሄደው ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ማግኝት ችየ ነበር ዘንድሮ ከጣሊያናዊቷ ቦክሰኛ ጋር ያደረኩት ግጥሚያ በሰከንዶች ውስጥ መጠናቁ ትኩረት እንድስብ ደረገኝ ሁኔታ ነበር ነገር ግን እኔ ሴት ነኝ የተወለድኩትም ሴት ሆኝ ነው” ብላለች፡፡
በፓሪሱ ኦሎምፒክ የመጀመርያ ግጥሚያ ጣሊያናዊቷን ተፎካካሪ በ46 ሰከንድ በበቃኝ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
በኢማን ምክንየት በየቀኑ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረባቸው የሚገኝኙት አወዳዳሪዎቹ በሰጡት ምላሽ በሰውነቷ ውስጥ የሚገኝው የቴስቴስትሮን መጠን በውድድሩ በሴት ምድብ ውስጥ እንዳትወዳደር የሚከለክላት አይደለም ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ማርክ አዳምስ ተወዳዳሪዋ የተወለደችውም ሆነ የኖረችው ሴት ሆና ነው አንዳንዶች እንደሚሉት ከጾታ ቅያሪ (ትራንስጀንደር) ጋር የሚያገናኝው ምንም ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
የፓሪሱን ኦሎምፒክ ውድድር ጨምሮ ተከታታይ 13 ግጥሚያዎችን ማሸነፍ የቻለችው እና ላለፉት ስምንት አመታት የቦክስ ውድድሮችን ስታደረግ የቆየችው ኢማን ከአራት ዓመታት በፊት በተደረገው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ተሳታፊ ነበረች።