በፓሪስ ኦሎምፒክ ያለ ፈቃዷ ዳሌ የነካው ግብጻዊ ስፖርተኛ ለእስር ተዳረገ
በፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገሩን ለመወከል ወደ ፈረንሳይ ያመራው ግብጻዊ በጾታዊ ትንኮሳ ተከሶ ዘብጥያ ወርዷል
ስፖርተኛው ከውድድር በጊዜ ቢሰናበትም ልምድ እንዲቀስም በሚል በፓሪስ እንዲቆይ ተፈቅዶለት ነበር ተብሏል
በፓሪስ ከተማ ያለ ፈቃዷ ዳሌ የነካው ግብጻዊ ስፖርተኛ ለእስር ተዳረገ።
የፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከ100 ዓመት በኋላ የኦሎምፒክ ውድድርን እያስተናገደች ትገኛለች።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብጽ በዚህ ውድድር እየተሳተፉ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ ስትሆን ነጻ ትግል ከምትወዳደርባቸው የስፖርት አይነቶች መካከል አንዱ ነበር።
ሞሀመድ ኤልሳይድ ደግሞ ሀገሩን በትግል ስፖርት ወክሎ ወደ ፓሪስ ኦሎምፒክ የመጣ ቢሆንም በጊዜ ከውድድሩ ተሰናብቷል።
የግብጽ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ስፖርተኛውን ወደ ሀገሩ ከመሸኘት ይልቅ ቀሪ ውድድሮችን እንዲያይ እና ልምድ እንዲቀስም በሚል በፓሪስ እንዲቆይ ፈቅዶለታል።
ይሁንና ይህ ስፖርተኛ ግብጻዊ በዛሬው ዕለት በፓሪስ ከተማ ባለ አንድ ካፍቴሪያ ውስጥ ለመዝናናት ጎራ ባለበት ወቅት የመስተንግዶ ሰራተኛዋን ዳሌ በእጁ መምታቱን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሰራተኛዋም ግብጻዊው ያለ ፈቃዷ ዳሌዋን በመምታት ጾታዊ ጥቃት እንደፈጸመባት መናገሯን ተከትሎ የፈረንሳይ ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሏል።
ይህ ግብጻዊም በቀጣት ክስ ይመሰረትበታል የተባለ ሲሆን እስራትም እንደሚጠብቀው ተገልጿል።
የግብጽ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በበኩል ስፖርተኛው ፈጽሞታል የተባለው ድርጊት አሳፋሪ መሆኑን ገልጾ ጉዳዩ በግብጻዊው መፈጸሙ ከተረጋገጠ የእድሜ ልክ እገዳ እንደሚጥልበት አስታውቋል።