ወደ ህዳሴው ግድብ ሲጓዙ የነበሩ “10 አሽከርካሪዎች ተገድለዋል” የሚለው መረጃ ሐሰት ነው-ሜጀር ጄነራል አስራት
በትናንትናው ዕለት ከ70 በላይ አሽከርካሪዎች በሰላም የጫኗቸውን እቃዎች ማድረሳቸውንም ጀነራሉ ተናግረዋል
ሜጀር ጄነራሉ የሕዳሴው ግድብ የ24 ሰዓት ጥበቃ ስለሚደረግለት ከማንኛውም ስጋት ነጻ መሆኑን ገልጸዋል
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሜጀር ጀነራል አስራት ዴኔሮ ለአል ዐአይን አማርኛ እንደተናሩት ወደ ህዳሴው ግደቡ እቃ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ “10 አሽከርካሪዎች ተገድለዋል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ ሐሰት ነው” ብለዋል።
ጄነራሉ “በትናንትናው ዕለት ከ70 በላይ አሽከርካሪዎች ወደ ህዳሴው ግድብ የተለያዩ እቃዎችን እና ማሽነሪዎችን” ያለምንም ችግር አድርሰዋል፡፡
ለግድቡ እቃዎችን እና ማሽኖችን በማጓጓዝ ላይ ነበሩ 10 አሽከርካሪዎች በመተከል ዞን ማንጎ ከተማ ላይ በታጣቂዎች ተገደሉ የሚሉ መረጃዎች በተለይም በማህበራዊ ሚዲያዎች በመሰራጨት ከዛሬ ጠዋት ጀመሮ ሲሰራጭ ቆይቷል፡፡
ጀነራሉ አክለውም “ወደ ካማሼ በመምጣት ላይ ያለ አንድ አይሱዙ በታጣቂዎች ተተኩሶበት ሹፌሩን ጨምሮ 3 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፤ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሀይል የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሁኔታውን ተቆጣጥሮታል” ሲሉም ተናግረዋል።
ታላቁ የህዳሴው ግድብ 24 ሰዓት ክትትል እና ጥበቃ የሚደረግለት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው ያሉት ሌተናል ጀነራል አስራት ፕሮጀክቱ ከማንኛውም የደህንነት ስጋት ነጻ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ከነበሩት የታጠቁ ሀይሎች ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት በተወሰደው እርምጃ እጅ ሰጥተዋል ገሚሶቹም ተመተዋል ያሉን ጀነራሉ ቀሪዎቹ በተበጣጠሰ መንገድ በመንቀሳቀስ ላይ በመሆናቸው ተከታትለን እጅ እንዲሰጡ እናደርጋለን እንቢ የሚሉትን ደግሞ እንመታቸዋለን ሲሉም ገልጸዋል።
በአካባቢው ከሱዳን አዋሳኝ መስመሮች አንስቶ የታጠቁ ሀይሎች የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በመምታት አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር ለማዋል በመሰራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚገኘው ሴዳል ወረዳ ”ሙሉበሙሉ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር” መዋሏንና ፖሊስን ጨምሮ ነዋሪዎች መሰደዳቸውን ገልፆ ነበር፡፡ ነገርግን ጄነራሉ ወረዳው “ሙሉበሙሉ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር” ውሏል የሚለውን መረጃ አስተባብለዋል፡፡