የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን መግለጫ “መሰረተ ቢስ” ሲል አጣጣለ
ኮሚሽኑ በክልሉ ከማሺ ዞን የሚገኘው የ“ሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የደረሱኝ መረጃዎች አመልክተዋል” ማለቱ የሚታወስ ነው
ክልሉ መግለጫው “በእውነታ ላይ ያልተመሰረተ እና ሊታረም የሚገባው ነው” ብሏል
የሰዳል ወረዳ “ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውሏል” መባሉ መሰረተ ቢስ ነው ሲል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ሰሞነኛ መግለጫ አጣጣለ፡፡
ክልሉ የኮሚሽኑን መግለጫ “ትክክል አይደለም፣ ሊታረም የሚገባው ነው” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን “በከማሺ ዞን የሚገኘውና ከ25 ሺህ በላይ ነዋሪዎች የሚገኙበት የሴዳል ወረዳ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ ከሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መዋሉን የደረሱኝ መረጃዎች አመልክተዋል” የሚል መግለጫን ከትናንት በስቲያ አውጥቶ ነበር፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያረጉት የክልሉ ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አቢዮት አልቦሮ “ኮሚሽኑ በአካባቢው ያልሆነን ነገር ነው በመግለጫ ያወጣው” ብለዋል፡፡
ትክክል እንዳይደለና “ሊታረም የሚገባው” እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
የክልሉ መንግስትም ሆነ የጸጥታ መዋቅሩ ይህን አለማለቱን በመጠቆም “መግለጫው ሚዛናዊነት የሚጎድለው ነው” ብለዋል፡፡
ኃላፊው ኮሚሽኑ በመግለጫው እንዳለው በአካባቢው ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ቡድን በወረዳው ጥቃት መፈጸሙን ግን አልሸሸጉም፡፡
“ቡድኑ የጉምዝን ህዝብ ነጻ አወጣለሁ በሚል በአካባቢው የሚንቀሳቀስ ጉህዴን (የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) የሚባል ታጣቂ ቡድን ነው” ያሉም ሲሆን “በተለያዩ የውጭ አካላት” እንዲሁም “ጁንታ” ባሉት የህወሓት ቡድን “የሚደገፍ” መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጉህዴን በካማሺ ብቻም ሳይሆን መተከልን በመሳሰሉ የክልሉ አካባቢዎች ጭምር እንደሚንቀሳቀስም ነው የተናገሩት፡፡
መተከል እና አካባቢው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገነባበት ስፍራ ነው፡፡
የቡድኑ በዚህ ትልቅ ሃገራዊ ፕሮጄክት ባለበት ስፍራ መንቀሳቀስም “አካባቢውን በጸጥታ ችግር እረፍት በመንሳት የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ነው” እንደ ኃላፊው ገለጻ፡፡
“ሰዳል ወረዳም የዚሁ እቅድ አካል ነው” ያሉት አቶ አቢዮት ባሳለፍነው ሰኞ ሚያዚያ 11 ቀን 2013 ዓ/ም ንጋት ላይ ቡድኑ በወረዳው ጥቃት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
በጥቃቱ የሰዎች ህይወት ያለፈም ሲሆን በርካቶች ቀያቸውን ለቀው ዳለቲን ወደመሳሰሉ አጎራባች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ሸሽተዋል፡፡
ቡድኑን ሲዋጋ የነበረው የክልሉ ልዩ ኃይልም የጥቃቱ ሰለባ ነው፡፡
ሆኖም ጉህዴን “ጥቃት ቢፈጽምም እንኳን ወረዳውን ሙሉ በሙሉ እንዳልተቆጣጠረ ነው የተናገሩት፡፡
ወረዳው አሁን በክልሉ ልዩ ኃይል እና በመከላከያ ሰራዊት ሙሉ ቁጥጥር ስር ይገኛልም ብለዋል፡፡
አቶ አቢዮት ታጣቂዎቹን ለማጽዳት በልዩ ኃይሉና በመከላከያው ዘመቻ (ኦፕሬሽን) በመደረግ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡
ዘመቻው እንደተጠናቀቀ የጠፋውን የሰው ህይወት ጨምሮ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳት እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል፡፡
አል ዐይን ጉዳዩን በተመለከተ ኮሚሽኑ ሊል የሚችለው ነገር እንዳለ ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡