የሞቱ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች መኖራቸውን ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ
በመተከል ዞን በሽፍቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ተናግረዋል
የችግሩ ዋነኛ መንስኤ የፖለቲካው መበላሸት እንደሆነ እና በሽፍቶች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል
የፌዴራል መንግስት በጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ የተደመሰሱ ከፍተኛ የሕወሓት አመራሮች መኖራቸውን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርኃኑ ጁላ አስታወቁ፡፡
በተደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ የሞቱ አመራሮች መኖራውን ለኢሳት ቴሌቪዥን የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ ይህም ወደፊትለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በተደጋጋሚ እያጋጠመ ያለውን የዜጎች ጭፍጨፋ ለማስቆም የመከላከያ ሠራዊት በሽፍታዎች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ጄኔራል ብርሃኑ ገለጻ ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮም ወደ መተከል የሄዱት ለዚሁ ተግባር ነው፡፡ እስካሁንም በርካታ ጸረ ሰላም ኃይሎች እርምጃ እንደተወሰደባቸው ጄኔራሉ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ይህ ሥራ በጸጥታ ኃይል ብቻ የሚሰራ እንዳልሆነና የፖለቲካ ስራ እንደሚጠይቅ ነው ያብራሩት፡፡ በአመራሮች መካከል ያለው የፖለቲካ ሽኩቻ ፣ መሬትህ ሊነጠቅ ነው በማለት የጉሙዝ ሽፍቶችን ማደራጀት እንዲሁም የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ ለአካባቢው ቀውስ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑም አንስተዋል፡፡ ይህም ነገሮችን እንዳወሳሰበ ነው ጄኔራሉ ያነሱት፡፡ ሽፍቶቹ እርምጃ ሲወሰድባቸው ጎረቤት ሀገር ጭምር እየሄዱ እንደሚሸሸጉም ጄኔራል ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
ነባሩ (Indigenous) ማሕበረሰብ እንዲሁም ‘ደገኛው’ የየራሳቸው ችግር እንዳለባቸውም የተናገሩ ሲሆን ‘ደገኛው’ መተከል የኛ ነው የሚል ፖለቲካ የማራመድ ከነባር ብሔረሰቦች ደግሞ የጉሙዝ ሽፍቶች ንጹኃንን የመግደል ተግባሮች እንደሚፈጸሙ ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ዋናው የፖለቲካው መበላሸት ስለሆነ ለዘላቂ መፍትሔ ፖለቲካዊ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዞኑ ፓዊ ከተማ ውይይት ካደረጉ በኋላ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ያነሱት ጄኔራል ብርሃኑ አሁን ላይ ሽፍቶች እየተደመሰሱ ስለመሆናቸውም ነው የጠቆሙት፡፡