የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በጅቡቲ እንዲነጋገሩ መጋበዛቸው ተገለጸ
የምስራቅ አፍሪካ የልማት ድርጅት ወይም ኢጋድ ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በጅቡቲ ለማወያያት እየተሯሯጠ ይገኛል
ስብሰባው እንዲካሄድ እቅድ የተያዘው ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት ጫና መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በጅቡቲ እንዲነጋገሩ በደብዳቤ ተጋብዘዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት ድርጅት ወይም ኢጋድ ሁለቱን የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በጅቡቲ ለማወያያት እየተሯሯጠ ይገኛል።
ከባለፈው ሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት 9ሺ ሰዎች እንዲገደሉ እና ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ስደተኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
የተለያዩ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የሱዳን ጦር መሪ እና የሉአላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ፕሬዝደንት ጀነራል አልቡርሃን በጅቡቲ ከመሀመድ ደጋሎ ወይም ሄሜቲ ጋር በሚቀጥለው ሀሙስ እንዲገኙ በኢጋድ ኃላፊ የግብዣ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል።
ውይይቱ ስለተኩስ አቁም እና የሰብአዊ እርዳታ መንገድ ክፍት ስለሚደረግበት ሁኔታ ሊያተኩር እንደሚችል የዲፕሎማት ምንጮች ለአል ዐይን ኒውስ ተናግረዋል።
ይህ ስብሰባ የሚካሄድ ከሆነ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከባለፈው ሚያዝያ ወር በኋላ በቡርሃን እና በሄሜቲ መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ይሆናል።
እነዚሁ ምንጮች እንደሚሉት ስብሰባው ጦርነቱ ቆሞ የፖለቲካ መፍትሄ በሚመጣበት ሁኔታዎች ላይ ይመክራል።
ስብሰባው እንዲካሄድ እቅድ የተያዘው ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ በአሜሪካ እና በሌሎች ሀገራት ጫና መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ሱዳንን ለሶስት አስርት አመታት የመሩት ኦመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ የሚመራ የሲቪል አስተዳደር ተቋቁሞ ነበር።
ነገርግን የሱዳን ጦር ጀነራሎች በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሰት አድርገው ስልጣን በብቸኝነት ተቆጣጠሩ።
ወታደራዊ ስልጣን ያየዙት ጀነራል ቡርሃን እና ሄሜቲ በመካከላቸው ግጭት ተቀስቅሶ፣ ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።