ቻይና፣ አሜሪካ እና ጃፓን በጸሀይ ቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ
ጃፓን ይህን ቴክኖሎጂ ቀድማ ለዓለም ለማስተዋወቅ 7 ቢሊዮን ዶላር ዶላር መመደቧን ገልጻለች
ሀገራቱ እየተፎካከሩ ያሉት ጸሀይ ካለችበት ቦታ ወደ ምድር ሀይል የማመንጨት ቴክኖሎጂን ቀድሞ ለመጠቀም ነው ተብሏል
ቻይና፣ አሜሪካ እና ጃፓን በጸሀይ ቴክኖሎጂ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው ተገለጸ፡፡
ለምድራችን ሙቀት በመስጠት የምትታወቀው ጸሀይ በርካታ ሀገራት ምድር ላይ ከጸሀይ ኤሌክትሪክን በማመንጨት እና በመጠቀም ላይ ሲሆኑ አሁን ደግሞ ተጨማሪ ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ለማዋል ሙከራዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
ጸሀይ ካለችበት ቦታ ሙሉ የጸሀይ ሀይልን ወደ ኤሌክትሪክ ሀይልነት መቀየር የሚያስችል ቴክኖሎጂን ለዓለም ለማስተዋወቅ አሜሪካ፣ ቻይና እና ጃፓን ፉክክር ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ኒኬይ እስያ ዘገባ ከሆነ አዲሱ ቴክኖሎጂ ጸሀይ ካለችበት ቦታ ሙሉ የጸሀይን ሀይል በገመድ አልባ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ወደ ምድር ሀይልን መላክ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመተግበር ከፈረንጆቹ 2015 ጀምሮ ሙከራ እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡
ሁለተኛው ሙከራ ደግሞ በ2018 የተተገበረ ሲሆን በ2025 ቴክኖሎጂውን እውን ለማድረግ ሀገራት ፉክክር ውስጥ እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ጃፓን ለዚህ ቴክኖሎጂ ውጤታማነት 7 ቢሊዮን ዶላር መመደቧን የገለጸች ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ የጸሀይ ሀይልን ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት አቅዳለች፡፡
ሌላኛዋ ተፎካካሪ ሀገር ቻይና ደግሞ እልህ አስጨራሽ ጥረት ላይ ናት የተባለ ሲሆን በዳመና እና በሌሊት ወቅት ሳይቀር የጸሀይ ሀይልን ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም ኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት የመጨረሻው ሙከራ ላይ መሆኗን አስታውቃለች፡፡
ከጸሀይ የሚገኘውን የጸሀይ ሀይልንም በስፋት ለሽያጭ ለማዋል አላማ ያደረገ ፕሮጀክቶችን በመተግበር ላይ መሆኗ የተገለጸው ቻይና በቅርቡ ሙከራውን እንደምታጠናቅቅ ይጠበቃልም ተብሏል፡፡
ሌላኛዋ የዚህ ቴክኖሎጂ ተፎካካሪ ሀገር አሜሪካ ስትሆን የካሊፎርኒያ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጸሀይ ከምትገኝነት ቦታ ያለውን ሙሉ ሀይል ወደ ኤሌክትሪክ ሀይልነት መቀየር የሚያስችል እና ከዚህ የሚገኘውን ሀይል ወደ ምድር መላክ የሚያስችል ገመድ አልባ ቴክኖሎጂ የሙከራ ስራ ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል ተብሏል፡፡
የአውሮፓ ህብረትም ዘግይቶ የቴክኖሎጂ ፉክክሩን የተቀላቀለ ሲሆን ባሳለፍነው ሚያዝያ ላይ የጸሀይ ሀይል ማመንጨት ስራዎችን ለማከናወን ከሁለት የጠፈር ቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡