እነዚህ መንትዮች ከዓመታት በፊት ለወላጅ እናታቸው ህጻናቱ እንደሞቱ ከተነገረ በኋላ በሀኪሞች እርዳታ እያንዳንዳቸው በ1ሺህ 400 ዶላር መሸጣቸውን አውቀዋል
ማህበራዊ ሚዲያን ይጠቀሙ...ምን አልባት መንታዎትን ያገኙ ይሆናል።
አኖ እና ኤሚ የተሰኙ ሴት ህጻናት በፈረንጆቹ 2002 ላይ ነበር በጆርጂያ የተወለዱት።
አሁን ላይ የ22 ዓመት ወጣት የሆኑት እነዚህ ወጣት እንስቶች በተለያየ ከተማ እየኖሩ ነበር።
በጆርጂያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ የዳንስ ውድድር ላይ አኖ የተባለችው እንስት የብዙዎችን ትኩረት የሳበ የዳንስ ችሎታዋን ማሳየቷን ተከትሎ ነበር ብዙዎች የወደዷት።
በእነ ኤሚ መኖሪያ ቤት ጎረቤት የሆኑ ሰዎች ስሟን ቀይራ ለምን እንደተወዳደረች ጥያቄ ያቀርቡላታል።
ይህን ተከትሎ ውድድሩን ዳግም ከተመለከተች በኋላ የተባለችው ልጅ እሷን እንደምትመስል ነገር ግን እሷ እንዳልሆነች ትናገራለች።
ይሁንና ይህን ጉዳይ በዚሁ ማቆም የከበዳት ኤሚ መከታተል ስትጀምር ተጨማሪ የዳንስ ቪዲዮ በቲክቶክ ሲሰራጭ ታያለች።
ይህች እሷን እምትመስለዋን ልጅ ማንነት ለማወቅ ብዙ ሙከራ ካደረገች በኋላ የመደዋወል እና ሌሎች መረጃዎችን መለዋወጥ ይጀምራሉ።
የሁለቱም ወላጆች ስለ ራሳቸው የነገሯቸው ታሪክ ተመሳሳይ መሆን፣ የመልካቸው እና ባህሪያቸው መመሳሰል ያስገረማቸው እነዚህ እንስቶች በአካል ተገናኝተው ጉዳዩን የበለጠ ለመመርመርም ይወስናሉ።
በመጨረሻም እነዚህ እንስቶች ወላጅ እናታቸው በወሊድ ወቅት እንደሞተች፣ እያሳደጓቸው ያሉት ወላጆችም አሳዝነዋቸው እነሱን ለመርዳት ብለው ከሆስፒታል እንደወሰዷቸው ይረዳሉ።
በነገሮች መገጣጠም ምክንያት ጥርጣሬ የገባቸው እነዚህ ተመሳሳይ እንስቶች ባደረጉት የተጠፋፉ ቤተሰቦችን በሚያገናኙ ድርጅቶች እገዛ አማካኝነት ወላጅ እናታቸው በህይወት በጀርመን ሀገር እንደምትኖር ይረዳሉ።
እናታቸውን በአካል ለማግኘት የፈለጉት እንስቶቹ በዚህ አገናኝ ተቋም እርዳታ በአካል ካገኙ በኋላ የተረዱት ነገር ወላጅ እናታቸው በወሊድ ወቅት በደረሰባት ድካም ከእንቅልፏ ስትነቃ መንታ ልጆችን እንደወለደች ነገር ግን እንደሞቱ በሀኪሞች እንደተነገራት፣ እድሜ ልኳንም በሀዘን እንዳሳለፈች መናገሯን ቢቢሲ ዘግቧል።
ቆይቶ በተደረገ ተጨማሪ ማጣራት እያንዳንዳቸው በ1 ሺህ 400 ዶላር ልጅ በጉዲፈቻ ለሚፈልጉ ቤተሰቦች መሸጣቸው ታውቋል።
መንትዮቹ ህጻናትም ከ22 ዓመት በፊት ለጉዲፈቻ አሳዳጊ ቤተሰብ የተለያየ እና የሀሰት መረጃ ተሰጥቷቸው ነበርም ተብሏል።