ከጭንቅላታቸው ተጣብቀው የተወለዱ መንትያዎችን 12 ሰዓት በፈጀ ቀዶ ጥገና ህክምና መለያየት ቻሉ
በቀዶ ጥገና ህክምናው ላይ ከእስራኤል እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ በርካታ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል
ከተወለዱ አንድ ዓመት የሞላቸው መንትዮቹ ከቀዶ ጥገና ህክምናው በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መተያየት ችለዋል
ከጭንቅላታቸው በጀርባ በኩል ተጣብቀው የተወለዱ ሴት መንትያ ህጻናት 12 ሰዓት በፈጀ ቀዶ ጥገና ህክምና መለያየት መቻሉ ተነግሯል።
ከተወለዱ አንድ ዓመት የሞላቸው መንትዮቹ በእስራኤል ሀገር በተደረገላቸው ቀዶ ጥገና ህክምና ለመጀመሪያ ጊዜ መተያየት መቻላቸውን ለእስራኤሉ ቻናል 12 ኒውስ ዘግቧል።
በቤርሽባ ከተማ በሚገኘው ሶሮካ የጤና ማእከል የተደረገው መንትዮቹን የማለያየት ቀዶ ጥገና ህክምና 12 ሰዓታትን የፈጀ መሆኑም ተነግሯል።
ቀዶ ጥገና ህክምናውን ለማካሄድ ከ1 ወር በላይ የፈጀ ዝግጅት ተደርጎ ነበር የተባለ ሲሆን፤ በህክምናው ላይ ከእስራኤል እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ በርካታ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰው ሴት መንትያ ህጻናቱ በአሁኑ ጊዜ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የህክምና ማእከሉ አስታውቋል።
ሶሮካ የጤና ማእከል የፒላስቲክ ቀዶ ህክምና ኃላፊ ለእስራኤሉ ቻናል 12 ኒውስ እንደተናገሩት፤ መንትዮቹ በአሁኑ ጊዜ በራሳቸው መመገብ እና መተንፈስ ላይ ይገኛሉ።
እንደዚህ ዐይነት የቀዶ ጥገና ህክምና በዓለም ላይ እስካሁን 20 ብቻ የተካሄደ ሲሆን፤ በእስራኤል ምድር ሲካሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።