ሃገራቸው የአውሮፓ ህብረት አባል ባለመሆኗ የተቆጡ ጆርጂያውያን ጠ/ሚ ጋሪባሽቪል ስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ
ይህን የተቃወሙ ጆርጂያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ ጋሪባሽቪል ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል
የአውሮፓ ህብረት ጆርጂያ ያቀረበችውን የአባልነት ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል
የጆርጂያ ዜጎች ሀገራቸው የአውሮፓ ህብረትን ልንቀላቀል ይገባል በሚል ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ ጋሪባሽቪል ስልጣን እንዲለቁ ጠየቁ፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረች አራት ወራት አልፎታል፡፡
የዩክሬን ኔቶን መቀላቀል ሉዓላዊነቴን ይጋፋል የምትለው ሩሲያ ዩክሬን ኔቶን እንዳትቀላቀል ብታስጠነቅቅም ዩክሬን በውሳኔዋ ገፍታ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባለች፡፡
በዚህ ምክንያትም ምስራቃዊ ዩክሬን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በሩሲያ ጦር እጅ ስር የወደቀ ሲሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዜጎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡
የቀድሞዋ የሶቪየት ህብረት አንድ አካል የሆነችው ጆርጂያ የአውሮፓ ህብረትን የመቀላቀል እቅድ እንዳላት በጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ ጋሪባሽቪል በኩል ጥያቄ አቅርባለች፡፡
የአውሮፓ ህብረትም የጆርጂያን ጥያቄ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ጥያቄው ውድቅ የተደረገው በሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪነት ምክንያት ነው በሚል ጆርጂያዊያን ተቆጥተዋል፡፡
ዛሬ በዋና ከተማዋ ትብሊሲ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ሀገራቸው የአውሮፓ ህብረትን በአባልነት እንድትቀላቀል ጠይቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢራክሊ ጋሪባሽቪል ባሳዩት ደካማ አመራር ምክንያት ስልጣን እንዲለቁም ነው ሰልፈኞቹ የጠየቁት፡፡
ኢራክሊ ጋሪባሽቪል ህብረቱ ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በቶሎ አሟልተው ልክ እንደ ዩክሬን እና ሞልዶቫ ሁሉ የእጩ አባልነት እድሉን ለማግኘት ቃል ገብተዋል፡፡
ህብረቱ እጩ አባል ላደረጋቸው ዩክሬን እና ሞልዶቫ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ጦር ከላከች በኋላ ስዊድን እና ፊንላንድ ኔቶን ለመቀላቀል ጥያቄ አቅርበው በሂደት ላይ ሲሆኑ ዩክሬን በበኩሏ የአውሮፓ ህብረት አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የህብረቱ እጩ አባል መሆኗ ይታወሳል፡፡
ዩክሬን በቀጣይ ህብረቱን በሙሉ አባልነት በይፋ እንደምትቀላቀልም ይጠበቃል፡፡