የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬን የምትገኘውን የሴቬሮዶኔስክ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ
95 በመቶ ያህሉ የምስራቃዊ ዩክሬን በሩሲያ እና በደጋፊዎቿ እጅ ወድቋል
ጦሩ በከተማዋ የራሱን አስተዳደር እያዋቀረ እንደሚገኝም ተነግሯል
የሩሲያ ጦር በምስራቃዊ ዩክሬን የምትገኘውን የሴቬሮዶኔስክ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረ።
ጦሩ የኢንዱስትሪ ከተማዋን ለመቆጣጠር ሳምንታትን የፈጀ ከባድ ውጊያን አድርጓል።
በስተመጨረሻም እንዲያፈገፍግ በታዘዘው የዩክሬን ጦር ላይ የበላይነትን ተቀዳጅቶ ከተማዋን ለመቆጣጠር ችሏል።
የሴቬሮዶኔስ በእጁ መውደቅ ለሩሲያ ጦር ትልቅ ስኬት ነው። በምስራቃዊ የዩክሬን አካባቢ ለማሳካት የሚያስበውን ግብ ለመምታት የሚያስችለው እንደሆነም ተነግሯል።
ሴቬሮዶኔስክ ሙሉ በሙሉ በሩሲያ ወታደሮች እጅ መውደቋን በቀጥታ በተላለፈ የቴሌቪዥን ስርጭት ያሳወቁት የከተማዋ ከንቲባ ኦሌክሳንድ ስትሪዩክ የራሳቸው የአስተዳደር መዋቅር ለመዘርጋት መቻላቸውን ተናግረዋል።
ኢንተርፋክስ የተሰኘው የሩሲያ ብዙሃን መገናኛም ወታደራዊ የመረጃ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ ይሄንኑ ዘግቧል።
የ100 ሺ ነዋሪዎች ባለቤት የነበረችው ሴቬሮዶኔስክ ከባድ ውድመት እንደደረሰባትም ነው የተነገረው።
በምስራቃዊ ዩክሬን ያለውን ወታደራዊ የበላይነት እያረጋገጠ የመጣው የሩሲያ ጦር
ከሴቬሮዶኔስክ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን ሊሲቻንስክ ከተማ ለመቆጣጠር በሚያስችል ግስጋሴ ላይ መሆኑም ተሰምቷል።
ሩሲያ እና ደጋፊዎቿ 95 በመቶ ያህሉን የምስራቃዊ ዩክሬን ግዛት ተቆጣጥረዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በሩሲያ እጅ የወደቁ የሃራቸውን ከተሞች እናስመልሳለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡