ጀርመናዊው ገርድ ሙለር ቀጣዩ የUNIDO ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመርጠዋል
አርከበ ዑቅባይ (ፒ.ኤች.ዲ) ለተባበሩት መንግስታት ኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/UNIDO/ ዋና ዳይሬክተነት ሳይመረጡ ቀሩ፡፡
በኢንዱስትሪ ልማት ስራዎች ላይ የካበተ ልምድ እንዳላቸው የሚታመንባቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አህመድ ልዩ የኢኮኖሚ አማካሪ በመሆንና በተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የኃላፊነት ስራዎች ላይ ያገለገሉት አርከበ ከጀርመኑ ገርድ ሙለር እና ከቦልቪያው በርናንዶ ካልዛዲላ ጋር ከፍተኛ ፉክክር ሲያደርጉ ነበር፡፡
ፉክክሩን አሸንፈው እንደሚመረጡ የብዙዎችን ቅድመ ግምት አግኝተው የነበረ ቢሆንም እንደታሰበው ሳይመረጡ ቀርተዋል፡፡
የጀርመን የፌዴራል የምጣኔ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር ቀጣዩ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ሙለር በዋና ዳይሬክተርነት የተመረጡት በተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ቦርድ አማካኝነት ነው፡፡
የቦርዱ ምርጫ የድርጀቱ ከፍተኛ አካል በሆነውና እንደፈረንጆቹ ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 3/2021 በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ይጸድቃል ተብሎም ነው የሚጠበቀው፡፡
አዲሱ ተመራጭ ጀርማናዊው የወቅቱ የኢኮኖሚያዊ ትብብር እና ልማት ሚኒስትር ገርድ ሙለር “ ከጠቅላላ ጉባኤው በኋላ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን መምራት ይችላል በሚል፤ ለተጣለበኝ እምነት እጅጉን አመሰግናለሁኝ ”ብሏል፡፡
ገርድ ሙለር “ዓለም አቀፍ ቀውሶችን ለማሸነፍ ጠንካራና ሁለንተናዊ ምላሽ ያስፈልጋል ፡፡ አሁን እያየነው ያለው ወረርሽኝ ለሁላችን የማንቂያ ደውል መሆኑን አምናለሁኝ፡፡በኮቪድ-19 እና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለሚደረግ ውጊያ በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሀገራት ታዳጊ ሀገራትን ለመደገፍ ከፍተኛ ቁርጠኝነትን ይጠይቃቸዋል፡፡ተጨማሪ ፈጠራዎች እና ኢንቨስትመንቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎች እና የእውቀት ሽግግር እንፈልጋለን፡፡ ግባችን ፍትሃዊ ግሎባላይዜሽን ፣ ዘላቂ የኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራ እና ለታዳጊ ሀገሮች የበለፀገ የወደፊት ዕይታ መፍጠር ነው” ሲሉም አክሏል፡፡
የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት/UNIDO/ አጀንዳ 2030፣ የፓሪስ ስምምነት፣ የባዮሎጂካል ዳይቨርሲቲ ስምምነት፣ ዘላቂ ልማት ግቦችና ሌሎች ዓለም አቀፍ ፕሮገራሞች ከመፈጸም አኳያ የመሪነቱ ሚና ሊጫወት ይገባል እንዲሁም ይችላልም ነው ያሉት ገርድ ሙለር፡፡
የበለጸጉ አካላት ለዚሁ ራኢይ እውን መሆን የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባቸውም ጭምር፡፡
ሙለር እንደፈረንጆቹ ከ2013 አንሰቶ የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን ሲመሩ የቆዩቱን ቻይናዊው ሊ-ዮንግን የሚተኩም ነው የሚሆነው፡፡