የተቋረጠው የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር አሜሪካ አሳሰበች
የአፍሪካ ቀንድ በወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝም ነው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ባወጣው መግለጫ የጠቆመው

በትግራይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ከአጋሮቿ ጋር እንደምትሰራም ዋሽንግተን ገልፃለች
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቋረጠው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ የድርድር ሂደት በአስቸኳይ እንዲጀመር አሜሪካ አሳሰበች፡፡
ዋሽንግተን ሰሞነኛውን የጄፍሪ ፌልትማንን የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት አስመልክታ በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት በኩል መግለጫ አውጥታለች፡፡
በመግለጫዋ የአፍሪካ ቀንድ በወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የጠቆመች ሲሆን በቀጣይ ሳምንታትና ወራት የሚተላለፉ ውሳኔዎች ለቀጠናው ህዝቦች ለራሷ ፍላጎቶች ጭምር ትልቅ እንደምታ እንደሚኖራቸው አስታውቃለች፡፡
የቀጠናው ቀውሶች ለመፍታት እንዲሁም ዜጎች ድመጻቸውን የሚያሰሙባትና መንግስታት ተጠያቂ የሚሆኑባት የበለፀገችና የተረጋጋች አፍሪካን እውን ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗንም ነው የገለጸችው፡፡
ሉዓላዊት እና አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ የዚሁ ራዕይ አካል ናትም ብላለች፡፡ ሆኖም አሁን ላይ በመላ ሀገሪቱ የሚስተዋለው የፖለቲካ እና የጎሳ ጽንፈኝነት እጅጉን እንደሚያሳስባት አልሸሸገችገም፡፡
በትግራይ እየተፈፀሙ ያሉ ግፍ እና ጭካኔዎች እንዲሁም ሰብአዊ ሁኔታዎች ተቀባይነት የላቸውምም ብላለች፡፡
በክልሉ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ለማቆም፣ የህይወት አድን እርዳታዎችን ለማድረግ እና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር እንደምትሰራም ነው አሜሪካ በመግለጫው ያስታወቀችው፡፡
በትግራይ ያጋጠመው ችግር ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሃገራዊ ለውጥ ለገጠሙት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ማሳያ ሆኖ በምልክትነት ሊጠቀስ እንደሚችልም ነው በቅርቡ የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒዮ ብሊንከን የተሾሙት ፌልትማን የገለጹት፡፡
ፌልትማን ለ10 ያህል ቀናት በነበራቸው የምስራቅ አፍሪካ የጉብኝት ቆይታ በግብጽ፣ኤርትራ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል፤ ከመሪዎች ጋርም መክረዋል፡፡
በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታ ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድና ሌሎችም ባለስልጣናት ጋር የመከሩ ሲሆን እየገጠሙ ያሉ ሃገራዊ ችግሮች በሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ መግባባት ላይ በሚያደርሱ፣ የሁሉም ኢትዮጵያ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብቶች በተከበሩባቸው ሁሉን አካታች መንገዶች ሊፈቱ እንደሚችሉ መወያየታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም የኤርትራ ኃይሎች በኢትዮጵያ መኖር ለእነዚህ ግቦች ተቃራኒ ነው ብለዋል፡፡ የኤርትራ ወታደሮች በቶሎ መውጣት የግድ ስለመሆኑ በአስመራ በነበራቸው ቆይታ ለፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አፅንዖት ሰጥተው መናገራቸውንም ነው የተናገሩት፡፡
ፌልትማን የሱዳንን ፖለቲካዊ ሽግግር በትውልድ የሚገኝና ለቀጣናው በዓብነት ሊጠቀስ የሚችል አንድ እድል ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡ የሽግግሩ መሪዎች የአሜሪካ ድጋፍ እንደማይለያቸውም ነው የገለጹት፡፡
በዚህም “ለሶስት አስርት ዓመታት ቀጣናውን ስታምስ የቆየችው ሱዳን ወደ ቀጣናው ቀዳሚ ተዋናይነት ልትመለስ ትችላለች”ም ብለዋል፡፡
ህዳሴውን ግድብ እና ድንበርን በመሳሰሉ አንኳር ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ከአጋሮቻችን ጋር መስራታችንንም እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
እንደ ጽ/ቤቱ መግለጫ ፌልትማን በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ከሶስቱ ሃገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውሃ እና በግድቡ ደህንነት እና አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ስጋት አለን ከሚሉት ከግብጽ እና ሱዳን መሪዎች ጋር መምከራቸውን የገለጹም ሲሆን ጉዳዩ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት በማከለ መልኩ በአፍሪካ ህብረት መሪነት መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚካሄደው ድርድር በአስቸኳይ ሊጀመር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በ2015ቱ የመርሆዎች ስምምነት መግለጫ (DoP) እና የአፍሪካ ህብረት ቢሮ ባሳለፍነው ክረምት የሰጠው መግለጫ ለድርድሩ መሰረት ሆኖ ያገለግላል በሚል እናምናለንም ነው መግለጫው የሚለው፡፡
አሜሪካ ለድርድሩ ስኬት ቴከረኒካዊ እና ፖለቲካዊ ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗንም አስቀምጧል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው በሌሎች ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮዎች ወደ ቀጣናው በቅርቡ እንደሚመለሱም ነው ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው ያስታወቀው፡፡