ላጃማኑ - “አሳ የሚዘንብባት” የአውስትራሊያ ከተማ
በታናሚ በርሃ አቅራቢያ የምትገኘው ላጃማኑ ባለፉት 50 አመታት አራት “የአሳ ዝናብ” ማስተናገዷ ተገልጿል
የከተማዋ ነዋሪዎች “ከሰማይ የወረዱት አሳዎች የፈጣሪ በረከቶች ናቸው” ብለዋል
መብረቅ አንዴ በወደቀበት ስፍራ በድጋሚ እንደማይወድቅ ይነገራል።
በአውስትራሊያ የምትገኘው ላጃማኑ ከተማ ግን “የአሳ ዝናብ” ደጋግሞ ተከስቶባታል ነው የተባለው።
በታናሚ በርሃ አቅራቢያ የምትገኘው ሞቃት ከተማ ባለፉት 50 አመታት አራት ጊዜ “አሳ ዘንቦባታል” ይላሉ የከተማዋ ነዋሪዎች።
በፈረንጆቹ 1974 ፣ 2004 እና 2010 አስደናቂውን ክስተት የመዘገበችው ከተማ በቅርቡም አራተኛውን ተመሳሳይ ሁነት ማስተናገዷን ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።
“ከባድ ውሽንፍርን ተከትሎ ዝንብ ሲጀምር የተለመደው አይነት ዝናብ መስሎን ነበር፤ ነገር ግን ወጥተን ስናይ አሳዎች መሬት እና ጣሪያ ላይ እየወደቁ ተመለከትን” ይላሉ አንድሪው ጆንሰን የተባሉ ነዋሪ ከኤ ቢ ሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ።
“ይህን አስደናቂ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተመለከትኩት፤ ከሰማይ የወረዱት አሳዎች የፈጣሪ በረከቶች ናቸው” ሲሉም አክለዋል።
ሚካኤል ሃመር የተባለ የአሳ ሃብት ጥበቃ ባለሙያ ግን “ከዚህ ቀደምም ሰዎች አሳ ዘነበ የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፤ ነገር ግን ሲዘንብ አላዩም፤ ምናልባትም በጎርፍ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ” በሚል ይሞግታሉ።
ሌሎች ባለሙያዎች ግን ላጃማኑ በርሃማ ከተማ መሆኗንና አሳዎች የሚከማቹበት ጉድጓዶች አለመኖራቸውን በማንሳት ሁነቱ ተአምር ቢመስልም ሊከሰት እንደሚችል ይገልጻሉ።
አሳዎቹ በከባድ አውሎ ንፋስ ከሌላ አካባቢ መጥተው ከዝናብ ጋር ወርደው ሊሆን እንደሚችልም በመጥቀስ።
ከዝናብ ጋር ወረዱ የተባሉት አሳዎችም በበርሃማዋ ከተማ የሚኖሩበት እድል እንደሌለ ነው የሚያነሱት።
ከሰማይ ከወረዱት አሳዎች ውስጥ አንዳንዶቹ እስትንፋሳቸው አለመቋረጡም ግርምትን መፍጠሩን ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።
በአውስትራሊያዋ ላጃማኑ ደጋግሞ የተከሰተው “የአሳ ዝናብ” ጉዳይ መነጋገሪያነቱ ቢቀጥልም በሆንዱራንስ በየአመቱ የሚያጋጥምና እየተለመደ የመጣ ነገር ነው ተብሏል።