አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶሪያ፣ ቱርክ እና አፍጋኒስታን ናቸው ተብሏል
ከ352 ሺህ በላይ ስደተኞች በጀርመን ጥገኝነት መጠየቃቸው ተገለጸ።
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚዋ ጀርመን ከፍተኛ ስደተኞች ወደ ግዛቷ እንደገቡ አስታውቃለች።
በ2023 ብቻ 352 ሺህ ስደተኞች ወደ ጀርመን ገብተው ጥገኝነት እንዲሰጣቸው አመልክተዋል ሲል ዶቸ ቪለ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ በ2022 በጀርመን ጥገኝነት የጠየቁ ጀርመናዊያን ቁጥር 111 ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል።
የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት ፣ የሶሪያ እና አፍጋኒስታን አለመረጋጋት ወደ ጀርመን የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር ከጨመሩ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው ተብሏል።
የስደተኞች ቁጥር መጨመርን ተከትሎም የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ መንግስት ላይ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
በጀርመን ስደተኛ ጠያቂዎች ታሪክ በ2016 722 ሺህ ሰዎች ጥገኝነት በመጠየቅ በታሪክ ከፍተኛው ዓመት ነበር።
የስደተኞች ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የጀርመን መንግሥት ስደተኖችን ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚያስችል ረቂቅ ህግ እያዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት ከአንድ ወር በፊት ወደ አውሮፓንየሚመጡ ስደተኞችን ለመገደብ አዲስ ህግ ያጸደቀ ሲሆን ይህም የተወሰኑ ሀገራት ላይ ጫና እንዳይበዛ እና ስደተኞችን ወደ ቀድሞ ሀገራቸው እንደሚመልስም አስታውቋል።