ጀርመን በሀገሯ ከሶስት ዓመት በላይ ለኖሩ ዜጎች ዜግነት ልትሰጥ ነው
በጀርመን ከ10 ዓመት በላይ የኖሩ ከ12 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ዜግነት አልተሰጣቸውም ተብሏል
አዲሱ ረቂቅ ህግ ሀገሪቱ የገጠማትን የሰራተኛ እጥረት ለመፍታት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል
ጀርመን በሀገሯ ከሶስት ዓመት በላይ ለኖሩ ዜጎች ዜግነት ልትሰጥ ነው፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን የዜግነት ህጓን ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ ህግ አዘጋጅታለች፡፡
አዲስ በተዘጋጀው ረቂቅ ህግ መሰረት በጀርመን በህጋዊ መንገድ አምስት ዓመት እና ከዛ በላይ ለኖሩ ዜጎች ዜግነት ማግኘት ያስችላል፡፡
ረቂቅ ህጉ በህጋዊ ስደተኝነት የሚኖሩ ዜጎች ለጀርመን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ከሆነ ሶስት ዓመት የኖሩ ዜጎችም ዜግነት ማግኘት ያስችላልም ተብሏል፡፡
በስራ ላይ ያለው የጀርመን የዜግነት ህግ አንድ ግለሰብ የጀርመን ዜግነትን ለማግኘት የግድ በህጋዊ መንገድ ስምንት ዓመት እና ከዛ በላይ መኖርን ይጠይቃል፡፡
ጀርመን የገጠማትን የሰራተኛ ፍላጎት ለመመለስ የዜግነት ፖሊሲዋን ለመከለስ እንደተገደደች የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ናንሲ ፌዘር ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶቸቪሌ ዘገባ አዲሱ ረቂቅ ህግ ዜጎች የብዙ ሀገራት ዜግነት እንዲኖራቸው የሚፈቅድ ሲሆን በጀርመን የተወለዱ ህጻናት ወላጆች አንዱ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ካለው የዜግነት ማስረጃ ይሰጠዋልም ተብሏል፡፡
ከ67 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው በጀርመን የሚኖሩ ህጋዊ ስደተኞች ደግሞ ጀርመንኛ ቋንቋን መናገርን እንደ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡
ይህ አዲስ ረቂቅ የዜግነት ህግ በቀጣይ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ውይይት እንደሚያረጉበት ይጠበቃል፡፡
አሁን ላይ ጀርመን ካላት 80 ሚሊዮን ህዝብ ብዛት ውስጥ 14 በመቶዎቹ የጀርመን ዜግነት የላቸውም የተባለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስት ሚሊዮን ያህሉ ከ10 ዓመት በላይ ኖረዋል፡፡