ጀርመን ጦሯን ለውጊያ ዝግጁ በማድረግ ላይ መሆኗን አስተሰወቀች
በጀት እና ወታደሮችን በማዋጣት ቀዳሚዋ የኔቶ አባል ሀገር አሜሪካ አንድ ቀን ጦሯን ከአውሮፓ ልታስወጣ ትችላለች ተብሏል
ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫን ካሸነፉ ለአውሮፓ ስጋት ይሆናል ተብሏል
ጀርመን ጦሯን ለውጊያ ዝግጁ በማድረግ ላይ መሆኗን አስተሰወቀች፡፡
የአውሮፓ ባለግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጦሯን ለውጊያ ዝግጁ የማድረግ እቅድ መንደፏን አስታውቀለች፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና አሜሪካ ከአውሮፓ ጦሯን ድንገት ልታስወጣ ትችላለች የሚለው ስጋት ጀርመን ጦሯን ዳግም ለማደራጀት ምክንያት እንደሆናት ተገልጿል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦር ወይም ኔቶ አባል የሆነችው ጀርመን የኢኮኖሚ አቅሟን ያህል ለጦሯ እያዋጣች አይደለም በሚል ስትተች ቆይታለች፡፡
በተለይም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጀርመን በአሜሪካ ጦር ኢኮኖሚዋን እያሳደገች ነው፣ እኛ ጦራችንን በጀርመን ስናሰማራ እሷ ግን ከተሞቿን እየገነባች ነው ሲሉ ተችተው ነበር፡፡
የጀርመን ወጣቶች ወደ መከላከያ ሰራዊት የመቀላቀል ፍላጎታቸው መቀነሱ ተገለጸ
በአሜሪካ ጦር ጥበቃ የሚያድግ የጀርመን ከተማ አይኖርም ያሉት ዶናልድ ትራምፕ አሁን ደግሞ ዳግም እንደሚመረጡ የቅድመ ምርጫ ውጤት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ዳግም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ በአውሮፓ ያሉ የአሜሪካ ወታደሮች ሊወጡ ስለሚችሉ ጀርመንን ጨምሮ የበርካታ ሀገራት ከተሞች ደህንነት አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ወደ ዩክሬን ግዘት የገባው የሩሲያ ጦር በቀጣይ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ግዛቶች ሊገባ ይችላል የሚለው ስጋት ጀርመንንም እንዳሰጋ ተገልጿል፡፡
የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት እና በቀጣይ ሊከሰቱ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች ጀርመንን አሳስቧል መባሉን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ጀርመን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጦሯን ለውጊያ በሚመጥን መልኩ እንደ አዲስ ለማደራጀት መወሰኗን የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴት አስታውቋል፡፡
የጀርመን ጦር ከሀገሪቱ ባለፈ ለአውሮፓ ደጀን በሚሆንበት መልኩ እንደ አዲስ ይደራጃል የተባለ ሲሆን የአየር፣ ምድር፣ ባህር ሀይል እና በይነ መረብ ሀይሏን እንደምታደራጅ ተገልጿል፡፡