ኦላፍ ሾልዝ ወደ ሩሲያ በኔቶ እና ሞስኮ መካከል እየተካረረ የመጣውን ውጥረት ለማርገብ ነው
የጀርመኑ መሪ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ሩሲያ አቅንተዋል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ እና ሩሲያ ጉዳዩን እንደማትቀበል በማሳወቋ በምስራቅ አውሮፓ ጦርነት ይቀሰቀሳል የሚል ስጋት ተደቅኗል፡፡
የሩሲያን ውሳኔ ተከትሎም የኔቶ አባል ሀገራት እንደ ተቋም እና እንደ አገር ከፍተኛ መጠን ያለው ጦር ወደ አካባቢው በማስፈር ላይ ሲሆኑ ሩሲያም ከ150 ሺህ በላይ ጦር ወደ ዩክሬን አስጠግታለች፡፡
በዚህ ምክንያትም በአካባቢው ጦርነት እንዳይቀሰቀስ የጠለያዩ አገራት ጉዳዩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ግፊት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ሞስኮ ተጉዘው ሩሲያ ዩክሬንን እንዳትወር ጉዳዩ በዲፕሎማሲ እንዲፈታ ለማግባባት ሞክረው ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡
አሁን ደግሞ የጀርመኑ መሪ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ወደ ሞስኮ የተጓዙ ሲሆን የጉዟቸው ዓላምም ኔቶ እና ሩሲያ በዩክሬን ጉዳይ የገቡበትን ውጥረት ማርገብ እንደሆነ የጀርመን ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
ኦላፍ ሾልዝ በትናንትናው ዕለት ወደ ዩክሬን መጥተው የነበረ ሲሆን ከሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ዘለንስኪ ጋር በውጥረቱ ዙሪያ ተወያይተው ነበር፡፡
በዛሬው የሞስኮ የአንድ ቀን ቆይታቸውም ከሩሲያ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚወያዩ የሚጠበቁት ኦላፍ ሾልዝ ሩሲያ ዩክሬንን እንዳትወር እና ጉዳዩ በዲፕሎማሲ ብቻ እንዲፈታ ለማግባባት እንደሚሞከሩ ይጠበቃል፡፡
ጀርመን የሩሲያ ዋነኛ የንግድ አጋር ስትሆን በዩክሬን ጉዳይ የዲፕሎማሲ ጥረቱ ካልተሳካ ጀርመንን እና አሜሪካንን ጨምሮ የአውሮፓ አገራት ጠንካራ ማዕቀብ እንደሚጣልባት አገራት ከወዲሁ በማስጠንቀቅ ላይ ናቸው፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ዩክሬንን የመውረር ሃሳብ እንደሌላት ገልጻ ዩክሬን ኔቶን ከተቀላቀለች የጸጥታ እና ደህንነት ስምምነት ግን ይኑረን ስትል በተደጋጋሚ በማሳወቅ ላይ ትገኛለች፡፡