የአማራ ክልል መንግስት ህወሃት በሰነዘረው ጥቃት በክልሉ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል አለ
አቶ አገኘሁ ከህወሃት ጥቃት ጀርባ “ሌሎች ኃይሎች“ እንዳሉ ገልጸዋል
ህወሃት በአማራ ክልል ጥቃት ከሰነዘረበት ዕለት ጀምሮ እስካሁን ከ500ሺ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል አስታወቀ
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር ዛሬ በሰጡት መግለጫ የህወሓት ቡድን በዋናነት በሶስት አካባቢዎች ማለትም በሰሜን እና በደቡብ ጎንደር እንዲሁም በሰሜን ወሎ ዞኖች ወረራ መፈፀሙን አስታውቀዋል፡፡ ቡድኑ ወረራ መፈጸሙን ተከትሎም በየደረሰባቸው ቦታዎች ሴቶችን መድፈሩን፤ የግለሰብና የመንግስት ንብረቶችን መዝረፉን እና ወጣቶችን አፍኖ መውሰዱን ተናግረዋል፡፡
የህወሓት ሃይሎች በደረሱባቸው ሶስት ዞኖች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ500 ሺህ በላይ መድረሱን ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ እንዲያደርግ አገኘሁ ተሻገር ጥሪ አቀርበዋል፡፡
ህወሃት፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከከፈተው ጥቃት ጀርባ “ሌሎች ኃይሎች“ እንዳሉ የገለጹት ርዕሰ መሥተዳድሩ፤ ሌሎች ያሏቸው ኃይሎችን ግን በዝርዝር አልገለጿቸውም፡፡ በርካታ የህወሃት አካላት የተዋጊነት፣ ዝርፊያ የመፈጸምና ሕዝብ የመበደል ስምሪት እንደተሰታቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸው ህወሃት፤ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ጎንደር ዞኖች አካባቢዎች ሰርጎ መግባቱንም አረጋግጠዋል፡፡
ቡድኑ፤ ጦርነቱን ህዝባዊ እንዳደረገው ያነሱት አቶ አገኘሁ፤ የአማራ ክልል ህዝብም በተመሳሳይ መንገድ ጦርነቱን ህዝባዊ እንዲያደርገው ተሻገር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አቶ አገኘሁ ጥቃት በተከፈተባቸው አካባቢዎች የተሰማሩት የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ እና የሌሎች ክልሎች ልዩ ኃይሎች እንዲሁም የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው የህወሃት ቡድን ላይ ወታደራዊ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ነገርግን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በአሻባሪነት የፈረጀው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ቦታዎችን መቆጣጠሩንና በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት አለማድረሱን መግለጹ ይታወሳል፡፡
በጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው “ህግ ማስከበር ዘመቻ” ተጀመረው ግጭት አሁን ላይ 11 ወራት ሊሆነው ነው፡፡
የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣ ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን ተከትሎ የህወሓት ሃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀሌን ጨምረው በርከታ ቦታዎች መቆጣጠር ችለዋል፡፡ትግራይን የተቆጣጠሩት የትግራይ ሃይሎች፤ ወደ አጎራባችና አማራና አፋር ክልል ጥቃት ከፍተው ቦታዎች ተቆጣጥረዋል፡፡
የህወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባቸው ክልሎች ጥቃት መክታቸውን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግስትና የፌደራል መንግስት የህወሓት ሃይሎችን ለመዋጋት የዘመቻ ጥሪ አቅርበዋል፤ጦርነትም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የህወሓት ሃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በማድረሳቸው ከ300ሺ በላይ ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸውንና የተናጠል ተኩስ አቁሞ የተፈለገውን ለውጥ አላመጣም ያለው የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊትና የክልል ልዩ ሃይሎች ጠንካራ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል፡፡