ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጀርመናውያን ሰራተኞች ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አዘዘች
ጀርመናውያን መምህራን እና የጎተ ኢንስቲትዩት ሰራተኞች ናቸው በቀጣዩ ወር ከሞስኮ የሚወጡት
ሩሲያ እና ጀርመን የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ግንኙነታቸው እየሻከረ ይገኛል
በሩሲያ የሚኖሩ ጀርመናውያን ሰራተኞች ከሩሲያ እንዲወጡ መታዘዛቸው ተነግሯል።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፥ ዲፕሎማቶች፣ መምህራን እና የጀርመን የባህል ተቋም (ጎተ) ሰራተኞች ናቸው ከሞስኮ እንዲወጡ ታዘዋል።
ሚኒስቴሩ ሩሲያ ምን ያህል ጀርመናውያንን እንዳባረረች ባይገልጽም በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሚሆኑ የጀርመን ድምጽ ዘግቧል።
ክሬምሊን በሞስኮ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲና የተለያዩ የሀገሪቱ መንግስታዊ ተቋማት ሰራተኞች ቁጥር እንዲቀነስ መወሰኑንም ዘገባው ያሳያል።
“ከሰኔ ጀምሮ ተፈጻሚ የሚሆነው ውሳኔ ጀርመን በሩሲያ የሚኖራትን ተሳትፎ የሚያመነምን ነው” ያለው የጀርመን የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት ውሳኔውን ተቃውሞታል።
ጀርመን በሚያዚያ ወር 2023 20 የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ማባረሯ የሚታወስ ነው።
ሞስኮም ለዚህ አጻፋውን ከመለሰች በኋላ የረጅም ጊዜ የንግድ አጋሮቹ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ይበልጥ እየሻከረ ሄዷል።
ዛሬ ለተሰማው የጀርመናውያን ሰራተኞች መባረር ዜና በርሊን የምትሰጠው ምላሽ ይጠበቃል።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የጀርመን እና ሩሲያን ግንኙነት ክፉኛ እየጎዳው ይገኛል።
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሾልዝ ጀርመን ሰራሹን ታንክ “ሊዮፓርድ 2” ወደ ኬቭ ለመላክ ሲያቅማሙ ቢቆዩም በምዕራባውያኑ ጫና አቋማቸውን መለወጣቸው ይታወሳል።
ዩክሬን ታውረስ የተሰኘውንና እስከ 500 ኪሎሜትር የሚወነጨፈውን ሚሳኤል እንድትሰጣትም በርሊንን መጠየቋ ተሰምቷል።