ጀርመን አዲስ የዜግነት ረቂቅ ህግ ይፋ አደረገች
ህጉ ሰዎች ለጀርመን ዜግነት በቀላሉ እንዲያመለክቱ ለማድረግ ያለመ ነው ተብሏል
የጀርመን መንግስት ባለፈው ዓመት የስደተኛ ህጉን ለማሻሻል ተስማምቷል
ጀርመን አዲስ የዜግነት ረቂቅ ህግ ይፋ አደረገች።
በርሊን ፍልሰትን ለማሳደግ እና በአውሮፓ ትልቁ ምጣኔ-ሀብቷ ውስጥ የስራ ገበያውን ለመክፈት እየፈለገች ባለችበት ወቅት የጀርመን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር ሰዎች ዜግነትን በቀላሉ እንዲያመለክቱ ለማድረግ ያለመ ረቂቅ ህግ አትሟል።
ረቂቁ የበርካታ ዜግነት ምርጫን ያቀረበ ሲሆን ዜግነት ከማግኘት በፊት የሚያስፈልገውን የመኖሪያ ጊዜ ከስምንት ዓመታት ወደ አምስት ወይም ሦስት ዓመት ዝቅ ያደርጋል ተብሏል።
ሮይተርስ እንደዘገበው 1950ዎቹ እና 60ዎቹ በስደተኛ ሰራተኝነት ወደ ጀርመን የገቡ (አብዛኞቹ ቱርኮች) ለዜግነት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ውስጥ የሆነው የጀርመን ቋንቋ ይነሳላቸዋል።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር ናንሲ ፌዘር በሰጡት መግለጫ "የማህበረሰባችን አካል የሆኑ ሰዎች ሀገራችንን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመቅረጽ እንዲረዷት እንፈልጋለን" ሲሉ እንደ ካናዳ ያሉ ሀገራትን በምሳሌነት ጠቅሰው፤ እርምጃው ጀርመን የምትፈልጋቸውን የሰለጠኑ ሰራተኞችን ለመሳብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
የጀርመን መንግስት ባለፈው ዓመት የስደተኛ ህጉን ለማሻሻል ተስማምቷል።
እ.አ.አ. በ2021 መጨረሻ ላይ ወደ 72.4 ሚሊዮን የሚጠጉ የጀርመን ዜግነት ያላቸው እና ወደ 10.7 ሚሊዮን የሚጠጉ የውጭ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በጀርመን ይኖራሉ።
ከእነዚህም ውስጥ 5.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ቢያንስ ለ 10 ዓመታት በጀርመን ውስጥ የቆዩ ናቸው።