የጀርመን አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ስራ አቁመዋል
የዶርትሙንድ፣ ኑረምበርግ እና ዱሴልዶርፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ናቸው ከአገልግሎት ውጭ የሆኑት
በግዙፉ የሉፍታንዛ አየርመንገድ ድረገጽ ላይ የተፈጠረው ተመሳሳይ ችግር ትናንት በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን ጉዞ ማስተጓጎሉ ይታወሳል
በጥቂቱ የሶስት የጀርመን አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች በዛሬው እለት ስራ ማቆማቸው ተነገረ።
የዶርትሙንድ፣ ኑረምበርግ እና ዱሴልዶርፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ናቸው ከአገልግሎት ውጭ የሆኑት።
በርካታ መንገደኞችን የሚያስተናግዱት የፍራንክፈርት፣ ሙኒክ እና በርሊን አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ግን ስራቸውን እንዳላቋረጡ ተገልጿል።
በሶስቱ አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ላይ የተፈጠረው ችግር ምክንያት እስካሁን አልተገለጸም።
የጀርመኑ ግዙፍ አየርመንገድ ሉፍታንዛ በትናንትናው እለት በገጠመው የአይቲ ችግር በሺዎች የሚቆጠሩ መንገደኞቹ በፍራንክፈርት ለስአታት መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
የዶርትሙንድ አውሮፕላን ማረፊያ ቃልአቀባይ፥ “ድረገጹ በመረጃ መንታፊዎች ጥቃት ሳይደርስበት አይቀርም” ብለዋል።
የጀርመኑ ተነባቢ ጋዜጣ ዴር ስፔግልም የሳይበር ጥቃት ሳይፈጸም እንዳልቀረ ነው የዘገበው።
አውሮፕላን ማረፊያዎቹ የገጠማቸውን ችግር በፍጥነት በመፍታት መንገደኞቻቸውን ለማስተናገድ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የአውሮፕላን መንገደኞች በድረገጾች ላይ የበረራ ስአታቸውን እንዳያዩ እና ትኬት እንዳይቆርጡ የሚያደርጉ የሳይበር ጥቃቶች ከዚህ ቀደም ደጋግመው ተፈጽመዋል።
በአሜሪካ ባለፈው ጥር ወር የአየር ትራፊክ አልታዘዝም በማለቱ ከ12 ሺህ በላይ በረራዎች መሰረዛቸው ይታወሳል።
በጥቅምት ወር 2022 ከ14 በላይ አውሮፕላን ማረፊያዎች ድረገጾች ተጠልፈው ለስአታት አገልግሎታቸው መስተጓጎሉም አይዘነጋም።
ለዚህ ጥቃት “ኪልኔት” የተሰኘው የሩሲያ የመረጃ መንታፊዎች ተጠያቂ ቢደረጉም ጥቃቱን ስለመፈጸማቸው ማረጋገጫ አልሰጡም።
በጀርመንም ዛሬ ለተፈጠረው ችግር የሩሲያውያን እጅ ሳይኖርበት እንደማይቀር ተገምቷል።
በርሊን ለዩክሬን “ሊዮፓርድ 2” የተሰኙ ታንኮችን እልካለሁ ማለቷ ሞስኮን ማስቆጣቱ የሚታወስ ነው፡፡