የዩክሬን ፕሬዝዳንት ለፈረንሳይና ጀርመን ጦርነቱን የሚቀይሩ' የጦር መሳሪያ እንዲያቀርቡ ተናገሩ
ፕሬዝዳንቱ የምዕራባውያን ለዩክሬን “የነጻነት ክንፍ” እንዲሰጡ አሳስበዋል
እስካሁን ድረስ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለኪየቭ ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ሀገር የለም
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በፓሪስ ጉብኝታቸው ፈረንሳይ እና ጀርመን ከሩሲያ ጋር በሚያደርጉት ጦርነት ከባድ መሳሪያዎችንና ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችን ወደ ዩክሬን ለመላክ ወደ ኋላ እንዳይሉ አሳስበዋል።
ዘለንስኪ ለሀገራቱ መሳሪያዎቹ “ጨዋታ ለዋጮች” የመሆን እድል እንዳላቸው ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመን መራሂ መንግስት ኦላፍ ሾልስ ጋር ለእራት ግብዣ ፓሪስ ገብተዋል።
በዕለቱ ቀደም ብለው ብሪታንያ የነበሩት ፕሬዝዳንቱ የምዕራባውያን አጋሮቻቸው ሞስኮን ለማሸነፍ የጦር አውሮፕላኖችን በመላክ ለዩክሬን “የነጻነት ክንፍ” እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ዛሬ ሀሙስ ወደ ብራሰልስ በማቅናትም የአውሮፓ መሪዎች ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።
"እኛ በጣም ትንሽ ጊዜ አለን። አሁን እየተናገርኩ ያለሁት ለሰላምና በሩሲያ የተጀመረውን ጦርነት ለማስቆም ስለሚያስፈልጉት መሳሪያዎች ነው" ሲሉ ዘለንስኪ ተናግሯል።
"ፈረንሳይ እና ጀርመን ጨዋታን የመቀየር አቅም አላቸው። እናም ንግግራችንን የማየው ከዚህ አኳያ ነው። በአፋጣኝ ከባድ የረጅም እርቀት መሳሪያዎችንና አብራሪዎቻችን ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ሲያገኙ የሩስያ ጥቃት በፍጥነት ያበቃል" በማለት እጣፈንታቸው ከሀገራቱ እጅ መሰንዘር ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ምዕራባውያን ሀገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ታንኮችንና የታጠቁ ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም የረጅም እርቀት የጦር መሳሪያዎችን ቃል ቢገቡም እስካሁን ድረስ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ለማቅረብ ፈቃደኛ የሆነ የለም።