ጀርመን ያለአሜሪካ ተሳትፎ በዩክሬን የሰላም አሰከባሪ ሀይል ለማሰማራት ፈቃደኛ አለመሆኗን አስታወቀች
በዩክሬን ጉዳይ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረጉት የአውሮፓ መሪዎች በሰላም አስከባሪ ስምሪት ጉዳይ መከፋፈል ውስጥ ገብተዋል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/18/243-124251-img-20250218-wa0006-1-_700x400.jpg)
በወታደራዊ ስምሪቱ ላይ ውዝግብ ውስጥ የገቡት መሪዎቹ የመከላከያ ወጪያቸውን ለማሳደግ ተስማምተዋል
የአውሮፓ ሀገራት በዩክሬን ሰላም አስከባሪ ሀይል ለማሰማራት በያዙት እቅድ ላይ ጀርመን እንደማትሳተፍ አስታወቀች፡፡
የአህጉሩ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት በርሊን አሜሪካ በስምሪቱ ላይ የማትሳተፍ ከሆነ ወታደሮቿን ወደ ቀጠናው እንደማትልክ ተናግራለች፡፡
ኤኤፍፒ ስማቸውን ካልጠቀሳቸው የጀርመን ባለስልጣን አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት ባለስልጣኑ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ደህንነት በሚለያዩባቸው ሁኔታዎች ውስጥ አንሳተፍም ብለዋል፡፡
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ በተመሳሳይ ሀገራቸው ለዩክሬን የምታደርገውን የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንደምትቀጥል አረጋግጠው በዩክሬን ምድር የሚልኩት ጦር እንደማይኖር ግን ገልጸዋል፡፡
የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ከድህረ ጦርነት በኋላ የኪየቭን ሰላም ለማረጋገጥ የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ለማዋጣት ባንጸባረቁት አቋም ጸንተዋል፡፡
ሩሲያ የዩክሬን ጦርነት የሚቆም ከሆነ ለግጭቱ ስር መሰረት የሆኑ ጉዳዮች በቅድሚያ ምላሽ ማግኘት እንደሚገባቸው በተደጋጋሚ አስታውቃለች፡፡
ከነዚህ ወሳኝ ነጥቦች መካከል የዩክሬንን የኔቶ አባልነት ውድቅ ማድረግ ፣ የምዕራባውያን ሀገራት እና የአውሮፓ ህብረት ወደ ምስራቅ እደረገ ያለው መስፋፋት እንዲገታ መጠየቋ ይጠቀሳል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሩስያ ተወካይ ቫዝሊ ኒቤንዚያ የሰላም አስከባሪ ሀይል የሚሰማራው በጸጥታው ምክር ቤት ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ያለምክርቤቱ እውቅና የሚደረግ ወታደራዊ ስምሪት በኢላማ ውስጥ ይገባል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በዩክሬን ሩስያ ጦርነት ምዕራባውን ሲከተሉት ከነበረው የተለየ ፖሊሲ ይዘው ብቅ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአውሮፓውን ስጋት ሆነዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከሳቸው በፊት እንደነበሩት ፕሬዝዳንት ጦርነቱን በገንዘብ እና ጦር መሳሪያ ከመደገፍ ይልቅ በድርድር መቋጨትን መርጠዋል፡፡
በዚህ ሂደት እስካሁን በነበረው ሁኔታ የጦርነቱ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩ የአውሮፓ ሀገራትን ገለል በማድረግ ከጦርነቱ ተሳታፊዎች ጋር ቀጥተኛ የግንኙነት መስመር በመዘርጋት ድርድር ለማስጀመር ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
አካሄዱ ያልተመቻቸው የአውሮፓ ሀገራት መሪዎችም በትላንትናው ዕለት በፓሪስ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገው ነበር፡፡
መሪዎቹ እነሱን ገለል አድርጎ ለዩክሬን ጦርነት መፍትሄ ለመስጠት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን ያህል የደህንነት ስጋት እንደሚሆንባቸው መክረዋል፡፡
በተጨማሪም ሩሲያ ዳግም በአውሮፓ ሀገር ላይ ጥቃት እንዳትሰነዝር ለማድረግ ፣ለዩክሬን ለአጠቃላይ አካባቢው ደህንነት ማስተማመኛ ይሆን ዘንድ የሰላም አስከባሪ በማሰማራት ዙሪያ እና በመከላከያ ወጪ ላይ ተወያይተዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሩሲያ እና አሜሪካ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን መካከል የሚደረገው ውይይት በዛሬው ዕለት በሳኡዲአረብያ ማካሄድ ይጀምራል፡፡