በሴቶች ላይ ከፍተኛ የቤት ውስጥ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሀገራት
በአለም ላይ 736 ሚሊየን የሚጠጉ ሴቶች በትዳር አጋሮቻቸው እና በቀድሞ የፍቅር ወዳጆቻቸው ጥቃት ይደርስባቸዋል
የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ለህክምና ፣ ለክስ ሂደቶች እና ተያያዝ ወጪዎች 3.6 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራን ያስተናግዳሉ
በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ በቤት ውስጥ እና በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጸም ጥቃት በአለም ጤና ድርጅት አሳሳቢ የማህበረሰባዊ የጤና እክል በሚል ተመድቧል፡፡
እንደ የአካባቢው እና ቀጠናው ሴቶች የሚደርስባቸው ጥቃት የተለያየ ቢሆንም ወሲባዊ ትንኮሳ ፣ ድብደባ ፣ አስገድዶ መድፈር ፣ ዛቻ እና ማስፈራርያን ጨምሮ ሌሎችንም ያጠቃልላል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት እና ዩኒሴፍ በጋራ ባስጠኑት ጥናት በአለም ላይ ከ736 ሚሊየን በላይ ሴቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ ናቸው፡፡
ጥናቱ ከ3 ሴቶች መካከል አንዷ በህይወት ዘመኗ ቢያንስ ለአንድ ጊዜ ይህ ጥቃት የሚፈጸምባት ሲሆን ከ4 ሴቶች መካከል አንዷ ደግሞ ከ15 አመቷ ጀምሮ ለዚህ ጥቃት የመጋለጧ እድል ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡
ጥቃቶቹ የተለያየ መልክ ሲኖራቸው የሚፈጸሙትም በፍቅር አጋሮች ወይም በትዳር ወዳጆች እንዲሁም በቀድሞ ፍቅረኞች ነው፡፡
የአለም ጤና ድርጅት ፣ ዩኒሴፍ ፣ ዩኤን ውመን እና ሌሎችም በሴቶች መብት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሴቶች ጥቃት ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ወንጀሎችን ለመከላከል የህጎችን መጥበቅ የወንጀለኞችን ተጠያቂነት ማጠናከር እንደሚገባ በተደጋጋሚ ይጠይቃሉ፡፡
የዚህ ጥቃት ሰለባ ሴቶች በአካል እና ስነልቦናቸው ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በዘለለ በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖንም እንደሚጋፈጡ ይነገራል፡፡
እንደ አለም ጤና ድርጅት መረጃም እነዚህ ሴቶች በጥቃቱ የሚደርስባቸው ጉዳት ለመታከም እና ጉዳት አድራሹን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም ለሌሎች ተያያዝ ወጪዎች በእድሜ ዘመናቸው በጋራ 3.6 ትሪሊየን ዶላር ኪሳራ ይደርስባቸዋል፡፡
በቤት ውስጥ እና ተያያዥ ጥቃት የሚደርስባቸው በርካታ ሴቶች ከሚገኙባቸው ሀገራት መካከል ባንግላዲሽ ቀዳሚዋ ስትሆን በሀገሪቱ 50 በመቶ ሴቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በአፍጋኒስታን ፣ ካናዳ እና ሳኡዲ አረብያ የሚገኙ ከ43 በመቶ - 46 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ይህን ጥቃት በመጋፈጥ በተከታዩ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡