ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ረጂም ጊዜ የሚያሳልፉት ለምንድን ነው?
ከ19 እስከ 55 አመት እድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ 92 በመቶ ወንዶች ከ20 ደቂቃ በላይ በመጸዳጃ ቤት ይቆያሉ
ህዳር 10/ የፈረንጆቹ ኖቬምበር 19 አለም አቀፍ የወንዶች ቀን እና የመጸዳጃ ቤት ቀን የሚከበርበት ነው
በተለምዶ ወንዶች ከሴቶች በበለጠ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ እንደሚያሳልፉ ይነገራል፡፡
በቅርብ ጊዜ የወጡ ጥናቶች ደግሞ ሁኔታውን ከተለምዶ ንግርት አውጥተው በእርግጥም ወንዶች በመጸዳጃ ቤት ውስጥ የሚያሳልፉት ጊዜ ከሴቶች እንደሚበልጡ አረጋግጠዋል፡፡
ሰማርት ስልኮች እና መሰል ቴክኖሎጂዎች ከመምጣታቸው በፊት ወንዶች ጋዜጣዎችን ይዘው መጸዳጃ ቤቶች ላይ መቀመጥ እንደሚያዘወትሩ የኒውዮርክ ፖስት ዘገባ ያመላክታል፡፡
በአስገራሚ ሁኔታ የዛሬው እለት ወይም በፈረንጆቹ ኖቬምበር 19 የአለም አቀፍ የወንዶች ቀን እና የመጸዳጃ ቤት ቀን የሚከበርበት ዕለት ነው፡፡
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው ወንዶች በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ፤ ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የብቸኝነት እና የዕለት ተዕለት ኑሮ ከሚያስከትለው ጫና እራስን ገለል ለማድረግ ከመፈለግ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ ወንዶች ጸጥ ባለ ሁኔታ ውስጥ ራሳቸውን ለማዳመጥ ፣ ሁኔታዎችን ለመገምገም ውሳኔዎችን ለመወሰን ጭምር የመጸዳጃ ቤት ቆይታቸውን እንደሚጠቀሙበት ነው የተጠቀሰው፡፡
ቫይስ የተሰኝው ድረ-ገጽ አንድ የጥናት ውጤትን ጠቅሶ እንዳስነበበው በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ወንዶች በመታጠቢያ ቤት ውስጥ በዓመት 7 ሰዓት ያህል የሚያሳልፉ ሲሆን ይህም ከጭንቀት ለመዳን እና ምቾትን ለማግኘት እንደሚጠቅማቸው መናገራቸውን ጠቅሷል፡፡
ከ19 እስከ 55 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወንዶች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት 92 በመቶ የሚሆኑት በመታጠቢያ ቤት ውስጥ እስከ 20 ደቂቃዎች እንደሚቀመጡ ተናግረዋል ።
70 በመቶዎቹ ከ 30 ደቂቃዎች ወይም ከ 40 ደቂቃዎች በላይ ሲያሳልፉ፤ 6 ሰዎች ደግሞ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ ለአንድ ሰአት እንደሚቀመጡ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በጥናቱ ምን ያህል ጊዜ በመጸዳጃ ቤት ውስጥ እንደሚያሳልፉ የተጠየቁ አስር ሴቶች በአማካኝ ከ10 ደቂቃ በላይ እንደማይቆዩ ነው የገለጹት፡፡
ወንዶች በመጸዳጃ ቤት ቆይታቸው በብዛት ምን አይነት ጉዳዮችን በማከናወን እንደሚያሳልፉ ሲጠየቁ በብዛት ከመለሷቸው መልሶች መካከል ለብቻ ሆኖ ከማሰብ እና ከማሰላሰል ውጪ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መመልከት፣ ኢሜይሎችን መቃኝት ፣ የሚወዷቸውን የተከታታይ ፊልሞች ክፍሎችን መመልከት ፣ መጽሐፍ ማንበብ እና የስልክ ጥሪዎችን በማድረግ እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡
ጥናቱ በመደምደሚያው ወንዶች ለመዝናናት እና ከችግሮች በተለይም በትዳር ውስጥ ግጭቶችን ለማስወገድ ብቻቸውን ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፤ ለአንዳንዶች መታጠቢያ ቤት ከዕለት ተዕለት ኑሮ ጩኸት ለማምለጥ እንዲሁም ምቾት እና የመረጋጋት ስሜትን ለማግኝት አስተማማኝ ቦታ ነው ብለው ያምናሉ ሲል አመላክቷል፡፡